በአዲስ አበባ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያስቀጥል አስቻይ ምኅዳር ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያስቀጥል አስቻይ ምኅዳር ተፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያስቀጥል አስቻይ የአሰራር ምኅዳር መፈጠሩን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ገለጹ።
በክልሉ የእምነት ተቋማት ለሰላምና ትውልድ ግንባታ ያላቸውን አበርክቶ ሊያጠናክሩ ይገባል
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ከዛሬ መጋቢት 02/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የሥራ አውደ ርዕይ ከፍቷል።
"የግል ዘርፍ ተሳትፎ፤ የብቁ ወጣቶች ማንሰራራት ለሀገር ልዕልና" በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀውን የሥራ አውደ ርዕይ ከ11 ሺህ በላይ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችና ሴቶች እንደሚጎበኙት ይጠበቃል።
የሥራ አውደ ርዕዩ 6 ሺህ የሚሆኑ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችና ሴቶች ቀጥተኛ ሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑበት መርሃ ግብር የሚያመቻች መሆኑ ተገልጿል።
አውደ ርዕዩን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከፍተውታል።
በዚሁ ጊዜ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ ከተማ ፈጣን የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድገት ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት መሰረት እየጣለ ነው።
ከተማ አስተዳደሩ ሥራ ፈላጊዎችን በማደራጀትና ከሥራ ቀጣሪዎች ጋር በማገናኘት የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያስቀጥል አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
በቴክኖሎጂ ዘርፍም ሥራ ፈላጊዎችና ቀጣሪዎችን የሚያገናኝ ምቹ ምህዳር መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።
በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለሶስት ቀናት የሚቆየው የሥራ አውደ ርዕይም የወጣቶችንና ሴቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማሻሻል ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን አንስተዋል።
የአዲስ አበባ የ24/7 የሥራ ባህልም የከተማዋን ልማትና ዕድገት በማስቀጠል የበርካታ ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ምክትልና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ኃላፊ አስፋው ለገሰ በበኩላቸው፤ በመዲናዋ በሰባት ወራት ውስጥ ከ280 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሥራ አውደ ርዕዩ የሚሳተፉ ከ200 በላይ ቀጣሪ ድርጅቶች የሚያስፈልጋቸውን የሰለጠነ የሰው ሃይል በመመልመል በርካታ ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።