ቀጥታ፡

በክልሉ የእምነት ተቋማት ለሰላምና ትውልድ ግንባታ ያላቸውን አበርክቶ ሊያጠናክሩ ይገባል

ዲላ፤የካቲት 30/2018 (ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የእምነት ተቋማት ለሰላምና ትውልድ ግንባታ ያላቸውን አበርክቶ ለማጠናከር በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ተመላከተ።

"የመደመር መንግሥት እና የኃይማኖት ተቋማት" በሚል መሪ ሐሳብ ከቤተ እምነት መሪዎች ጋር የውይይት መድረክ በዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የሚገኙ የኃይማኖት ተቋማት ብዝሃነትን በማክበር ለሰላም መጽናትና ለልማት መጠናከር የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ሊያጠናክሩ ይገባል።

ክልሉን የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች ውጤታማ መሆናቸውን አውስተው መንግሥት እና የኃይማኖት ተቋማት ተቀናጅተው በመስራት ልማትና ሠላምን ማፅናት እንደሚችሉ በተግባር ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ይህንን አጠናክሮ በማስቀጠል የክልሉን ልማትና ብልፅግና ለማፋጠን የሚደረጉ ጥረቶችን የኃይማኖት ተቋማት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ የእምነት ተቋማት ለሰላምና ትውልድ ግንባታ ያላቸውን አበርክቶ ለማጠናከር በትብብርና በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።


 

የኃይማኖት ተቋማት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን ሚና በመገንዘብ በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ናቸው።

ከኃይማኖት ተቋማት ጋር ተቀራርቦ መስራት የዞኑን ልማት እንደሚያፋጥን አንስተው ይህንንም ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ፤ የሃይማኖት ተቋማት ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያን ስለሰላም በማስተማር ትውልድን በፍቅር የማነጽ ቀዳሚ ኃላፊነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ ለሀገር ልማት እና እድገት መፋጠን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ ኡስታዝ አብዱራህማን ወርቁ ናቸው።

የክልሉ የእምነት ተቋማት አስተምህሮን ከማስረፅ ባለፈ ለሰላምና ልማት መጠናከር በትብብር እየሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል።

የጌዴኦ ዞን የወንጌል አማኞች ካውንስል ዋና ጸሐፊ አገልጋይ በጸጋ ጂዳ በበኩላቸው የሃይማኖት ተቋማት ከመንፈሳዊ አስተምህሮታቸው ባለፈ ዜጎችን በስነ-ምግባር በማነጽና ለሀገር ግንባታ በማዘጋጀት ረገድ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም