ቀጥታ፡

ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጎላ ሚና አለው

ጎንደር ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን በማሳደግ ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት ተገለፀ።

በኢትዮጵያ 30 ሚሊዮን ሴቶችን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ ያለመ ንቅናቄ ተጀመረ

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ቀኑ ቢያድጉ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ አካል የሆነውን ፋይዳ የዲጂታል መታወቂያን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው።


 

በዚህም በዞኑ 280 ሺህ ሴቶች ፋይዳ የዲጂታል መታወቂያን በማውጣት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።፡

ፋይዳ መታወቂያ ሴቶች የፋይናንስና ሌሎች የመንግስት አገልግሎቶችን በዲጂታል አሰራር በተቀላጠፈ መንገድ እንዲያገኙ በማድረግ ጊዜን፣ ጉልበትንና እንግልትን መቀነሱን አስረድተዋል።

በተለይም በገጠሩ ክፍል የሚገኙ ሴቶች በመሬት ነክ ጉዳዮች ላይ ይገጥማቸው የነበረውን የፍትህ እጦት ለማስተካከል ያስቻለ መሆኑንም አመልክተዋል።

 በዞኑ የምእራብ ደንቢያ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሰናይት ማሩ ፤ ፋይዳ የዲጂታል መታወቂያ በመንግስት ተቋማት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት እንድችል አግዞኛል ብለዋል፡፡

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የማክሰኚት ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ብርቱካን ማንደፍሮ በበኩላቸው፤ ፋይዳ የዲጂታል መታወቂያ እኔንና ቤተሰቤን የጤና መድህን ተጠቃሚ በማድረግ ቀልጣፋ አገልግሎት እንድናገኝ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮልናል ብለዋል።

በዞኑ በዘንድሮ ዓመት 725 ሺህ ሴቶችን የፋይዳ መታወቂያ ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ መያዙን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም