በኢትዮጵያ 30 ሚሊዮን ሴቶችን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ ያለመ ንቅናቄ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ 30 ሚሊዮን ሴቶችን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ ያለመ ንቅናቄ ተጀመረ
ሮቤ፤ የካቲት 29/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ 30 ሚሊዮን ሴቶችን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ ያለመ ሀገር አቀፍ የምዝገባ ንቅናቄ በባሌ ሮቤ ከተማ ተጀመረ።
"በሀገርሽ ታወቂ" በሚል መሪ ሀሳብ የምዝገባ ንቅናቄውን ዛሬ ያስጀመሩት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራምና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር በመተባበር ነው።
በንቅናቄ መድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂክማ ኬይረዲን እንዳሉት የሴቶችን ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው።
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና የንብረት ባለቤትነት መብት ለማረጋገጥ ከሚያግዙ አስቻይ ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።
"ፋይዳ ለሴቶች ከመታወቅም በላይ ነው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በተለይ የሴቶችን መብትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ እንዲረጋገጥ አስተዋጾው የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት።
በተለይ ሴቶች ሰርተው ለመለወጥ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ከመንግስት የሚፈልጉትን የገንዘብ ብድር አቅርቦትና የፋይናንስ ስርዓት ለማቀላጠፍ መታወቂያው አይነተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ለጤናና ለፍትህ አገልግሎት እንዲሁም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ያስችላል ብለዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ ባለፉት ሁለት ወራት በሴቶች ላይ በተሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሀገር የፋይዳ መታወቂያ ተመዝጋቢ ሴቶች ቁጥር ቢጨምረም ለማሳካት ከተያዘው ግብ አንጻር ብዙ መሥራት ይጠይቃል ።
ዛሬ በተጀመረው ንቅናቄም 30 ሚሊዮን ሴቶችን በማስመዝገብ የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ ግብ መያዙን ጠቁመው ለንቅናቄው ውጤታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዮዳሄ አርዓያስላሴ በበኩላቸው፤ ዲጂታል መታወቂያ ማንኛውም ዜጋ የራሱን ማንነት የሚገልጽበት መለያ ነው፡፡
የሴቶች የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ ንቅናቄ ዓላማም በመጪው ሰኔ ወር እንደሀገር አጠቃላይ የተመዝጋቢዎችን ቁጥር 90 ሚሊዮን ለማድረስ የተያዘውን ግብ ለማሳካት መሆኑን ገልጸዋል።
የሴቶች ፋይዳ መታወቂያ ምዝገባና ብሔራዊ የምዝገባ መርሃግብር የማይነጣጠሉ እንደሆነ የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ እስካሁን ድረስ የፋይዳ መታወቂያ ተመዝጋቢ ዜጎች ቁጥር 37 ሚሊዮን መድረሱን አክሏል።
ከአጠቃላይ ተመዝጋቢዎች ቁጥር 60 በመቶ ወንዶችና ቀሪዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ዛሬ የተጀመረው የንቅናቄ መድረክ 30 ሚሊዮን ሴቶችን ለመመዝገብ ያለመ መሆኑንም አስረድተዋል።
በባሌ ሮቤ ከተማ የተጀመረው የንቅናቄ መድረክ በቀጣዮቹ ሰባት ቀናት በመላ አገሪቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።
የሮቤ ከተማ ከንቲባ ዲኖ አሚን፤ የብሔራዊ መታወቂያ የንቅናቄ መድረክ እንዲሳካ በየደረጃው የሚገኙ የከተማዋ አመራሮች የሴቶችን ግንዛቤ በመፍጠር የበኩላቸውን እንዲወጡ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የኢትዮጵያ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ስነምህዳርን ለመገንባት በዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 1284/2015 መሠረት የተደራጀ ፕሮግራም ነው።