ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ባለፉት ሰባት ወራት ከ4 ሺህ 488 ኪሎ ግራም የሚበልጥ የተጣራ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓል

ጋምቤላ ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል ባለፉት ሰባት ወራት ከ4 ሺህ 488 ኪሎ ግራም የሚበልጥ የተጣራ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት አስታወቀ።

በክልሉ የግብርና አቅምን በመለየት የተከናወኑ የአሰራር ማሻሻያዎች ውጤት አምጥተዋል

ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለው የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ትግበራ ሀገሪቷ ያላትን ሀብቶች በአግባቡ በማልማት ለህዝብ ጥቅም ለማዋል እያስቻለ ነው።

መንግስት የተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ደግሞ በተለይም በማዕድን ዘርፉ ያሉት ሀብቶች ተለይተው እንዲለሙ ከማድረግ ባለፈ በህጋዊ መንገድ ለዓለም ገበያ እንዲቀርብና ከዘርፉ የሚገኘው ጥቅም እንዲሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ይታወቃል።

የጋምቤላ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ገዳሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር የብዝሃ ኢኮኖሚ ተብለው ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየለሙ ከሚገኙት ዘርፎች መካከል አንዱ የወርቅ ማዕድን ነው።

ይህንንም ታሳቢ በማድረግ በክልሉ ባለፉት ሰባት ወራት በተከናወኑ ስራዎች በዘርፉ ስኬታማ ውጤቶች ተመዝግበዋል።


 

ባለፉት ሰባት ወራት ከ4 ሺህ 488 ኪሎ ግራም በላይ የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ ገቢ የተደረገ ሲሆን ይህም ከእቅዱ በ988 ኪሎ ግራም ብልጫ ያለው መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ለብሔራዊ ባንክ ገቢ የተደረገው የወርቅ ምርት መጠን ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር  ከ1 ሺህ 175 ኪሎ ግራም በላይ ብልጫ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ የተደረገው የወርቅ ምርት በክልሉ ዲማ፣ አቦቦ፣ ጋምቤላና መንጌሽ ወረዳዎች በባህላዊ መንገድ፣ በልዩ አነስተኛና በትላልቅ የወርቅ ኩባንያዎች የተመረተ ነው ብለዋል።

ባለፉት ወራት ከቀዳሚው ዓመት ብልጫ ያለው የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ሊደረግ የቻለው መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የቁጥጥር፣ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች በመከናወናቸው መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም እንደ ሀገር በመንግስት የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለወርቅ ምርት መጨመር ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይም በክልሉ የተጀመሩ ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከር በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው ከ6 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማስገባት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም