ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተከናወነ ባለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመረዳዳት ባህል እየተጠናከረ መጥቷል 

ወላይታ ሶዶ፤ መጋቢት 1/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተከናወነ ባለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በርስ የመረዳዳት ባህል እየተጠናከረ መምጣቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ተናገሩ፡፡

በክልሉ የሃይማኖት ተቋማት ለሰላምና ለልማት መጠናከር የሚወጡትን ሚና ሊያጎለብቱ ይገባል

ርዕስ መስተዳድሩ በጽህፈት ቤታቸው አማካኝነት በወላይታ ሶዶ ከተማ ለወላይትኛ ሙዚቃ ተጫዋች አርቲስት ፍሻሌ ሚልካኖ የተገነባውን መኖሪያ ቤት ከሙሉ የቤት ቁሳቁስ ጋር አስረክበዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲያስጀምሩ ለአርቲስቱ በገቡት ቃል መሠረት የመኖሪያ ቤቱ መገንባቱም ተመልክቷል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ መኖሪያ ቤቱን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን የመደገፍ ተግባር ባህል እየሆነ መጥቷል።


 

ለአርቲስቱ የተገነባው የመኖሪያ ቤትም በአጭር ጊዜ መጠናቀቁን ገልጸው ''ከተባበርን በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ከችግራቸዉ ማውጣት እንችላለን'' ብለዋል።

አርቲስት ፍሻሌ ሚልካኖ ለህዝብ አንድነትና ልማት በጥበብ ስራው በርካታ አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን በመጠቆም ሌሎች አርቲስቶችም የእሱን ፈለግ በመከተል ለሀገር በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል።


 

የክልሉ መንግስትም በተለያዩ ዘርፎች እየተጉ ያሉ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን የመደገፉን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለጹት፡፡

የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማርያም በበኩላቸዉ፤ አርቲስቱ የወላይታን ባህልና ታሪክ ለዓለም እንዲተዋወቅ እንዲሁም የህዝቦችን አንድነት በመስበክ ከፍተኛ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።


 

ለአርቲስቱ የመኖሪያ ቤት በመገንባቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው የከተማ አስተዳደሩም በመሰል ችግሮች ውስጥ ያሉ ወገኖችን የመደገፉን ስራ እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።


 

አርቲስት ፍሻሌ ሚልካኖ በበኩሉ፤ ስለተደረገለት በጎ ተግባር አመስግኖ በቀጣይ ለአገር አንድነት መጠናከር እያደረገው ያለውን አስተዋጽኦ እንደሚቀጥልም ነው የገለጸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም