በክልሉ የሃይማኖት ተቋማት ለሰላምና ለልማት መጠናከር የሚወጡትን ሚና ሊያጎለብቱ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሃይማኖት ተቋማት ለሰላምና ለልማት መጠናከር የሚወጡትን ሚና ሊያጎለብቱ ይገባል
ሆሳዕና፤መጋቢት 1/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ለሰላምና ለልማት መጠናከር የሚወጡትን ሚና ሊያጎለብቱ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።
በሆሳዕና ከተማ "በመደመር እይታ የሃይማኖት ተቋማት ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ከእስልምና ሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን ጋር ክልል አቀፍ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት የለውጡ መንግስት ሀገርን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች በማሳተፍ መጠነ ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ለሀገረ መንግስት ግንባታ የሚበጁ፣ በስነ-ምግባር የታነጹና ሀገር ተረካቢ ዜጎችን በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ድርሻ እየተወጡ መሆኑንም ገልጸዋል።
በቀጣይም የተጀመሩ የሰላምና የልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የሃይማኖት ተቋማቱ ከመንግስት ጋር ያላቸውን ትብብር አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
"ተቋማቱ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የእድገት ደረጃ ወደ ላቀ ምዕራፍ በማሸጋገር ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብ የሚጠበቅባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል።
የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ በበኩላቸው በህዝቦች መካከል አብሮነትን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሃይማኖት ተቋማት ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ረገድ የሃይማኖት መሪዎች ግንባር ቀደም መሆን እንዳለባቸውም አንስተዋል።
የክልሉን የብዝሃ ሃይማኖት፣ ቋንቋና ባህል ጸጋ በመጠቀም ለልማት ማዋል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመድረኩ ላይ በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የክልል አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ነው።