አብሮነትን ለሚያጠናክሩ ጉዳዮች ትኩረት እንሰጣለን- የኃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
አብሮነትን ለሚያጠናክሩ ጉዳዮች ትኩረት እንሰጣለን- የኃይማኖት አባቶች
ሆሳዕና ፤ መጋቢት 1/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አብሮነትን በሚያጠናክሩና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ የእስልምና ሀይማኖት አባቶች ገለፁ፡፡
ትውልዱ በሀገር ሰላምና ልማት ውስጥ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር የድርሻችንን እንወጣለን- የሀይማኖት አባቶች
''በመደመር መንግሥት እይታ፣ የኃይማኖት ተቋማት ሚና'' በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የእስልምና ኃይማኖት አባቶችንና የእምነቱ ተከታዮችን ያካተተ ክልል አቀፍ የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሄዷል፡፡
የእምነቱ አባቶች በዚሁ ወቅት ፤ በክልሉ አብሮነትን በሚያጠናክሩና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ብለዋል፡፡
በስልጤ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ አብዱረሂም አህመድ እንዳሉት፤ የሁሉ ነገር መሰረት የሆነውን ሰላም አስጠብቆ ማስቀጠል ከሀይማኖት አባቶች የሚጠበቅ በጎ ተግባር ነው፡፡
በዞኑ ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር በመከባበር ላይ የተመሰረተ አካሄድን መከተል በሚያስችሉ አስተምህሮዎች ላይ በማተኮር እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኃይማኖት ልዩነት የጥላቻ መንስኤ ሊሆን እንደማይገባ አመልክተው፤ አብሮነትን በሚያጠናከሩና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ከቀቤና ልዩ ወረዳ የተገኙት ሼህ ነስሩ አርጋኒ በበኩላቸው፤ የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ ከሁሉም ቤተ እምነቶች ጋር አብሮነትን ማጠናከር እንደሚያዝ ነው የተናገሩት።
የእምነቱን አስተምህሮ ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ያለብንን ከፍተኛ ኃላፊነት ለመወጣት እንሰራለን ነው ያሉት።
በተጨማሪም በክልሉ መንግሥት እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን በመደገፍ ለአካባቢው ፈጣን እድገት በትብብር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡
የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ በህጃ አብዱልጀሊል በበኩላቸው፤ የለውጡ መንግሥት ሙስሊሙ ማህበረሰብ በሰላም ግንባታና በልማት ስራዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ምቹ መደላድል መፍጠሩን ገልፀዋል።
ይህንኑ መሰረት በማድረግም ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር በሰላም ግንባታ ላይ በትብብር በመስራት በክልሉ የተጀመረውን ለውጥ አጠናክረን ማስቀጠል ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር፣ ጉድለቶችን በምክክር በመፍታት እና በጋራ ለማደግ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል፡፡