ቀጥታ፡

ትውልዱ በሀገር ሰላምና ልማት ውስጥ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር የድርሻችንን እንወጣለን- የሀይማኖት አባቶች

ወላይታ ሶዶ ፤መጋቢት 1/2018 (ኢዜአ) :- ትውልዱ በሀገር ሰላምና ልማት ውስጥ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኃይማኖት ተቋማት መሪዎች ተናገሩ።

"የመደመር መንግስትና የሃይማኖት ተቋማት" በሚል መሪ ሃሳብ በወላይታ ሶዶ ከተማ በተካሄደ መድረክ ላይ የተሳተፉ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት መሪዎቹ በሰጡት አስተያየትም በሃገር ሰላምና ልማት ላይ የድርሻውን የሚወጣ እና ስብዕናው የተገነባ ትውልድ ለማፍራት ኃላፊነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የወላይታ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መላከ ሰላም ቀሲስ ቦኪቻ ኤንጋ፤ ቤተክርስቲያኗ ለሀገር ሰላም፣ እድገትና ልማት የድርሻዋን ስትወጣ መቆየቷን ጠቁመዋል።

በተለይም ምዕመናንን በማነጽና በማስተማር፣ ስብዕናው የተገነባ ዜጋ ማፍራትን ጨምሮ በሀገረ መንግስትና በሰላም ግንባታ ላይ አበክራ እየሰራች ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተመዘገበ ያለው እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው በየአካባቢው ሰላም እንዲጸና ጥረታቸውን እንደሚያጠናክሩም ገልጸዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ሼህ ሚፍታ ከማል በበኩላቸው፤ የዜጎችን አብሮነትና አንድነት በሚያጎለብቱ ተግባራት ላይ በትኩረት እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።

''እስልምና ማለት ሰላም ነው፤ በሰላም እሴት ግንባታ እና በልማት ተባብሮ መቆም ለሀገር የማንሰራራት ጉዞ ስኬታማነት ወሳኝ ነው'' ሲሉም ገልጸዋል።

ተባብሮ በመስራት የውስጥ አንድነትና የሰላም እሴቶችን ከማጠናከር ባለፈ በጋራ የመኖር እሴትን እንደሚያጎለብትም ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ሰብሳቢ መጋቢ ስልጣኑ ሽፈራው፤ ካወንስሉ የሀገርና የህዝብ አንድነትን በሚያመጡ፣ ሰላምና ልማትን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ  እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

''በስነ-ምግባር የታነፀ ትዉልድ በማፍራት በሀገሪቱ ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲመዘገብ የድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል'' ሲሉም ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም