በግብርናው ዘርፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በግብርናው ዘርፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2018(ኢዜአ)፦በግብርናው ዘርፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በክልሉ የግብርና ምርምር ውጤቶች ለተጠቃሚው በመድረሳቸው በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት እየመጣ ነው
የግብርና ሚኒስቴር "በሴቶች ላይ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ ለሀገር ብልጽግና መሰረት ነው" በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን (ማርች 8) በፓናል ውይይት እና በተለያዩ ኹነቶች አክብሯል።
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ የጀርባ አጥንት በሆነው ግብርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የሀገርን ምርታማነት ከማሳደግ አኳያ የሴቶች ሚና ወሳኝ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ግብርና እና የሴቶች ተሳትፎ የማይነጣጠሉ በመሆናቸው በዘርፉ የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
ሴቶችን በቴክኖሎጂ እና በፋይናንስ ተደራሽ ማድረግ፣ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው መስራት፣ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚያሳድጉ ስራዎችን በትኩረት ማከናወን ሚኒስቴሩ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ኸይረዲን በበኩላቸው፣ መንግስት ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራትም የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ገነት አብደላ፤ ሴቶች ለሀገር እድገትና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ሴቶችን ማብቃትና መደገፍ የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባልም ብለዋል፡፡
በሚኒስቴሩ ቅጥር ግቢ የተገነባው የህጻናት ማቆያ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን ሴት አምራቾች ምርቶቻቸውን ለገበያ ያቀረቡበት ልዩ ኤግዚቢሽንም ተከናውኗል።