የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ህብረተሰቡ በልማት ስራዎች የሚያደርገውን አስተዋጽኦ እንዲያጎለብት መነቃቃት ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ህብረተሰቡ በልማት ስራዎች የሚያደርገውን አስተዋጽኦ እንዲያጎለብት መነቃቃት ፈጥሯል
ሐረር፤ መጋቢት 1/2018(ኢዜአ)፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሀረሪ ክልል ጉብኝት በክልሉ በለውጡ ዓመታት የተከናወኑ የልማት ሥራዎች እየሰጡት ያለው ጥቅም በተግባር የተረጋገጠበት እና ህብረተሰቡ ለልማቱ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ እንዲያጎለብት መነቃቃት የሚፈጥር ነው ሲሉ የሐረር ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።
የአዲስ አበባ የልማት ስኬቶች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና አይቀሬነት የሚያረጋግጡ ናቸው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐረሪ ክልል የተከናወኑ የኮሪደር ልማት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን ትናንት ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ሌሎች የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሐረር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች፤ ጉብኝቱ የልማት ሥራዎች በተግባር ለዜጎች እየሰጡት ያለውን ጠቀሜታ የተመለከቱበትና በቀጣይ ለላቀ ሥራ የሚያዘጋጅ ነው ብለዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል መምህር ደረጀ ተስፋዬ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የፕሮጀክቶችን ክንውን እንዲሁም ለህዝብ እየሰጡት ያለውን አገልግሎት የገመገመ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በቀጣይም የልማት ሥራዎች በተሻለ ፍጥነት እንዲከናወኑና ህብረተሰቡም የሚያደርገውን አስተዋጽኦ እንዲያጎለብት ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የከተማና የገጠሩን ገጽታ እየቀየረው መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይም የክልሉን እድገት ለማፋጠን በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ የሐረር ከተማን ውብና ጽዱ ከማድረግ ባለፈ ለነዋሪዎችና ጎብኚዎች ምቹ ማድረጉን የተናገሩት ደግሞ አቶ ደመቀ ካሳዬ ናቸው።
በክልሉ በልማት ሥራዎችና በአገልግሎት አሰጣጥ የታየው ተጨባጭ ለውጥ በህብረተሰቡ ዘንድ ደስታ እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት መነቃቃት በመፍጠር ይህን ተግባር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ያስችላል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያደረጉት ጉብኝት ለአካባቢው ተስፋን የሰነቀና ልማት እንዲጠናከር መነቃቃትን የፈጠረ ነው ያለችው ደግሞ ወጣት ሄለን ሲራጅ ናት።
"በተለይ የኮሪደር ልማት ለወጣቶች የሚፈጠረውን የሥራ ዕድል ያሰፋና ተጠቃሚነትን እያጎለበተ ነው" ያለችው ወጣቷ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐረር የልማት ሥራዎችን በመጎብኘታቸው ምስጋና አቅርባለች።
በክልሉ ሶፊ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ማወርዲ ሙህየዲን በበኩሏ "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አካባቢያችን መጥተው መጎብኘታቸው ለገጠሩ ማህበረሰብ ያላቸውን ከፍተኛ ትኩረት ያሳያል፤ በዚህም ተደስቻለሁ" ብላለች።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በየአካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለወጣቶች ተስፋን መሰነቁን ተናግራለች።