የእናቶች እና ህጻናትን ጤና ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት አስመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
የእናቶች እና ህጻናትን ጤና ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት አስመዝግበዋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2018(ኢዜአ)፦ የእናቶች እና ህጻናትን ጤና ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገባቸውን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
የጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር የህክምና ግብዓቶችንና መሳሪያዎችን መደገፍ የሚያስችል የሶስት ዓመት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።
በሸገር ከተማ የጤና ተቋማትን ለማስፋፋት በተከናወኑ ተግባራት ውጤት እየተገኘ ነው
በስምምነቱ መሰረት ከአጋር አካላት ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የሚቆይ የ282 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ግምት ያለው የህክምና ግብዓት ድጋፍ ይደረጋል፡፡
ይህ ድጋፍ የእናቶች፣ የህፃናት እና የቤተሰብ ምጣኔ ግብዓት አቅርቦት ማሳደግ የሚያስችል ሲሆን የሕክምናውን ዘርፍ ለማዘመን የተጀመሩ ስራዎችን የሚያጠናክር ነው ተብሏል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋትም አመርቂ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በመንግስት በጤና ተቋማት ለእናቶች የሚሰጠው የቅድመ ወሊድ እና የድህረ ወሊድ ነፃ የህክምና አገልግሎት ለዚህ እመርታ ትልቅ ሚና መጫወቱን ተናግረው ለመንግስት ቁርጠኝነት መሳካት የማህበረሰቡ እና የአጋር አካላት ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር ሚኒስትሯ አክለዋል።
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ክርስቲን ፐረን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ወሳኝ አጋር ሀገር መሆኗን ጠቁመው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የጤና ትብብር እየጠነከረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ በእናቶችና ህፃናት ሞት ቅነሳ ያስመዘገበችውን ውጤት ለማበረታታት የታለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌሎች የአጋር ድርጅት ተወካዮችም በመንግስት በኩል የጤናውን ዘርፍ ጥራትና ተደራሽነት ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት በቁርጠኝነት እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።