በሸገር ከተማ የጤና ተቋማትን ለማስፋፋት በተከናወኑ ተግባራት ውጤት እየተገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ የጤና ተቋማትን ለማስፋፋት በተከናወኑ ተግባራት ውጤት እየተገኘ ነው
ሸገር፤ መጋቢት 1/2018(ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ የጤና ተቋማትን በማስፋፋትና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት ውጤት እየተገኘ መሆኑን የከተማው ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አበራ ቦቶሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማው የጤና ተቋማት ተደራሽነትን ለማስፋትና ለህብረተሰቡ ዘመናዊ የጤና አገልግሎት ለመስጠት በጥናት ላይ የተመሰረቱ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በከተማው የጤናውን ዘርፍ ውጤታማ ለማደርግ የግንባታና የማስፋፊያ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቅሰው በተሰራው ስራ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
በተለይም የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ተደራሽነትን ማሳደግ፣ ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ስርጭትን ማረጋገጥ፣ የፋይናንስ አጠቃቀምን ማሻሻልና አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ ማስደገፍ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
በተሰሩ ስራዎችም በከተማ አስተዳደሩ በ2015 ዓ.ም የነበሩት 24 የጤና ተቋማት በአሁኑ ወቅት ወደ 35 ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም በሸገር ከተማ ደረጃ ሆስፒታል እንዳልነበረ አስታውሰው፣ በአምስት ዓመት ውስጥ አምስት ሆስፒታሎች ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
በዚህም አንድ ሆስፒታል ግንባታው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን እንዲሁም ሁለት ሆስፒታሎች ደግሞ በቅርብ ጊዜ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ይሆናሉ ብለዋል።
በተመሳሳይ ኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ እና በገፈርሳ ጉጄ የሚገነቡት ሆስፒታሎች ግንባታቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ተጨማሪ አዳዲስ የጤና ኬላዎች ግንባታ መከናወኑንና ቁጥራቸውም ወደ 85 ከፍ ማለቱን ጠቁመው በከተማው ለሚገኙ 46 ነባር ጤና ኬላዎች እድሳት መደረጉን ናኃላፊው ገልጸዋል።
የመድኃኒት አቅርቦት ችግርን ለመፍታትም የማህበረሰብ ሞዴል ፋርማሲዎችን በማስፋፋትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ በኩል ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።
በአጠቃላይ ባለፉት ሦስት ዓመታት በጤናው ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት የከተማዋ የጤና ተቋማት ሽፋን ከነበረበት 33 በመቶ ወደ 53 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል።