ቀጥታ፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተጣለባቸውን ሃገራዊ ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣት በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 30 /2018(ኢዜአ)፦የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መንግሥትና ሕዝብ የጣለባቸውን ሃገራዊ ኃላፊነት ለመወጣትና ትርጉም ያለው ውጤት ለማስመዝገብ በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ።

የምገባ መርሃ ግብር በተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻል እንዲመጣ አስተዋፅኦ እያደረገ ነው

የትምህርት ሚኒስቴር ለሁለት ቀናት የሚቆይ የ2018 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቁልፍ ተግባራት ላይ የግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው። 


 

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምርምሮችን በማከናወንና ብቁ ዜጋን በማፍራት ረገድ ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ተቋማቱ አሁን ካለው ዓለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ በልዩ ትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከአመራር እስከ ታችኛው የሥራ ክፍል የተቀናጀ ርብርብ ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ ተቋማቱ ለሃገር ዕድገት እያበረከቱ ያሉትን አስተዋጽኦ ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሸኔ በበኩላቸው፤ ተቋማቱ በሥራ ባሕልና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ መሻሻል ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡


 

በዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ሥራዎች መሻሻል እያሳዩ መሆኑን ጠቅሰው የትምህርት ተደራሽነትና አካታችነትን ከማረጋገጥ ባለፈ በምርምር ጥራት ላይ በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ 

ግምገማው ተቋማቱ ከሚኒስቴሩ ጋር በገቡት ውል መሠረት ያከናወኗቸውን ተግባራት እና ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች በጥልቀት ለመለየት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህ መድረክ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት፣ የሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶችና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም