ቀጥታ፡

የምገባ መርሃ ግብር በተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻል እንዲመጣ አስተዋፅኦ እያደረገ ነው

ሰመራ፤ የካቲት 30 /2018(ኢዜአ)፦ የትምህርት ቤቶች  የምገባ መርሃ ግብር ማህበራዊ መረጋጋት በመፍጠር በተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻል እንዲመጣ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ተናገሩ።

እመርታ ቤተ-መጻሕፍት በአንድ ጊዜ ለ1 ሺህ ሰው አገልግሎት መስጠት ይችላል - የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

11ኛው የአፍሪካ የትምህርት ቤት የምገባ መርሃ ግብር "የትምህርት ቤት ምገባ ለተማሪዎች ተሳትፎና ውጤታማነት አይተኬ ሚና አለው" በሚል መሪ ሐሳብ በሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር በአሰቦዳ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከብሯል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ እንደተናገሩት፤ የትምህርት ቤት የምገባ መርሃግብር ማህበራዊ መረጋጋት በመፍጠር በተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻል አሳይቷል።

መርሃ ግብሩ በተለይም አነስተኛ የገቢ ምንጭ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች እፎይታ የሰጠና የተማሪዎች የትምህርት አቀባበልና ጤንነት ላይ ለውጥ እያመጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ ከማድረግ ባሻገር የትምህርት ፍላጎታቸው እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በመርሃ ግብሩ ከ8 ሚሊዮን በላይ ህፃናት ተጠቃሚ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ የመስኖ ስራን በማጠናከር መርሃ ግብሩን ለማገዝ የጀመረውን የእርሻ ስራ ሌሎች ክልሎችም በአብነት ወስደው መተግበር እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአፋር ክልል ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ወጣቶች ባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀሚድ ዱላ በበኩላቸው፤ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር የነገ ተስፋ የሆኑ ህፃናትን የወደ ፊት ዕጣ ፈንታ ያመቻቸ ነው ብለዋል።


 

በተለይም እንደ አፋር ክልል በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ተግዳሮት ለሚያጋጥማቸው አካባቢዎች  ምላሽ መስጠት የቻለ አዎንታዊ ፋይዳ ማበርከቱን አብራርተዋል።

በመርሃ ግብሩ ለትምህርት ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ በአፋር ክልል የትምህርት ምጣኔ እንዲሻሻል አስተዋፅኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሳ አደም በበኩላቸው፤ የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር የተማሪዎች የመማር ፍላጎት እንዲጨምርና በተረጋጋ ሁኔታ ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ አግዟል።


 

በአካልና አዕምሮ ዕድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኀላፊዎች፣ የግብረ ሰናይ ድርጅት ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም