የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና ተምሳሌታዊ ተግባር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና ተምሳሌታዊ ተግባር ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና (Climate-smart agriculture) አርአያ የሚሆን ስራ እያከናወነች እንደምትገኝ የዓለም ባንክ ከፍተኛ የግብርና ባለሙያ ቲም ሮበርትሰን ገለጹ።
ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና (Climate-smart agriculture) ሁሉን አቀፍ እይታ ያለው የግብርና ምርታማነት አማራጭ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አስተማማኝ የግብርና ሥርዓት መገንባት ይጠበቅባቸዋል
ይህ የአሰራር ዘዴ የግብርና ምርታማነት ብቻ ሳይሆን ለአደጋዎች የማይበገር አቅም መገንባትና ለአየር ንብረት ተስማሚ መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።
ድርቅን የሚቋቋሙ ሰብሎችን ማምረት፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የስንዴ ምርታማነት፣ የኢትዮጵያ የማዳበሪያ እና የጤናማ አፈር ፍኖተ ካርታ፣ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን የመስኖ ስራዎች ማስፋትና የተራቆቱ መሬቶችን በአካባቢ ጥበቃ ስራ ወደ ነባር ይዞታቸው መመለስ ከተከናወኑ ተግባር መካከል ይጠቀሳሉ።
የዓለም ባንክ ከፍተኛ የግብርና ባለሙያ ቲም ሮበርትሰን ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና እየገነባች ያለችው አቅም የሚደነቅ መሆኑን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና ስኬታማ ስራዎችን እያከናወነች እንደሚገኝ ጠቅሰው እንደ አረንጓዴ አሻራ ባሉ ኢኒሼቲቮች የቀጣናው ሀገራት ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የዘርፉ ስኬቶች ለማስፋት መንግስት፣ ቀጣናዊ ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይበልጥ ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጣናው የሚገኙ ሀገራት በአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና ያላቸውን አቅም የበለጠ ማጠናከር እንደሚኖርባቸውም ነው ባለሙያው የገለጹት።
በዚህ ረገድ የዓለም ባንክ ከመንግስታት ጋር የግሉ ዘርፍ በአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና ያለውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግና በተለይም ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢኖቬሽን፣ ዲጂታል መፍትሄዎች፣ ዘላቂ የኢነርጂ አጠቃቀም እና ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርናን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም ነው ያነሱት።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዓለም የግብርና ፋይናንስ ከፍተኛ ለውጥ ማሳየቱን ገልጸው ሀገራት ፋይናንስ በዘላቂነት የሚያመጡ አጋርነቶችን መፍጠር እንዳለባቸው መክረዋል።
ለዚህ ተቋማት ትስስራቸውን ማጠናከር፣ አማራጭ ፋይናንስ መፈለግ፣ እሴት መጨመር ትኩረት መስጠት እና ለጋራ ግብ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።