ቀጥታ፡

እመርታ ቤተ-መጻሕፍት በአንድ ጊዜ ለ1 ሺህ ሰው አገልግሎት መስጠት ይችላል - የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2018 (ኢዜአ)፡- ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር መጻሕፍት ሽያጭ እና ከድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር በተገኘ በጀት የተገነባው እመርታ ቤት-መጻሕፍት በአንድ ጊዜ ለ1 ሺህ ሰዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚችል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በድሬዳዋ የሚገኘውን እመርታ ቤተ-መጻሕፍት ጎብኝተዋል።

የድሬ የኮሪደር ልማት የተሻሻለ የአካባቢ ውበት እውን እንዲሆን አስችሏል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ይህን ተከትሎም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ባጋራው መረጃ፤ ቤተ-መጻሕፍቱ ከ1 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የቦታ ስፋት ላይ ማረፉን ገልጿል።

ዘመናዊ መሠረተ-ልማት እንዲኖረው ተደርጎ መገንባቱንም አስታውቋል።


 

ሦስት የወለል ብዛት የያዘው ቤተ-መጻሕፍቱ፤ አገልግሎቱን ለሚፈልጉ ተስማሚ የሆነውን የድሬን አየር እያገኙ እንዲገለገሉ የቴራስ ቦታ ተዘጋጅቶለታል ብሏል ጽሕፈት ቤቱ።




‎ቤተ- መጻሕፍቱ የብሬል ማንበቢያ ቦታ፣ ለልዩ ፍላጎት ተጠቃሚዎች የተዘጋጀ የአይቲ ማዕከል፣ ከክፍል ውጭ የንባብ ቦታ፣ የግልና የቡድን ማንበቢያ እና የጥናት ክፍሎች እንዲሁም የኮንፈረንስ ክፍልን አካቷል ብሏል። 


 

በአጠቃላይ እመርታ ቤተ-መጻሕፍት በአንድ ጊዜ ለ1 ሺህ ሰው አገልግሎት መስጠት እንዲችል ሆኖ የተገነባ መሆኑንም ነው የገለጸው።


 

በመጽሐፍ መደርደሪያው ላይ ብቻም 1 ሚሊየን መጻሕፍትን የመያዝ ዐቅም እንዳለው አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም