የኃይማኖት ተቋማት በሰላም ግንባታ አስተዋጿቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የኃይማኖት ተቋማት በሰላም ግንባታ አስተዋጿቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ወላይታ ሶዶ ፤ የካቲት 30 /2018(ኢዜአ)፦የኃይማኖት ተቋማት የወንድማማችነት ትርክትን በማስረጽ ለሰላም ግንባታ እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ ሊያጠናክሩ ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አስታወቁ።
በክልሉ ከኃይማኖት ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት ፈጣን እድገት ለማስመዝገብ የተጀመረው ተግባር ይጠናከራል
"የመደመር መንግስትና የኃይማኖት ተቋማት" በሚል መሪ ሃሳብ በወላይታ ሶዶ ከተማ የኃይማኖት ተቋማት የውይይት መድረክ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ነው ።
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት፤ የኃይማኖት ተቋማት የዜጎችን ስብዕና በመቅረጽ ሀገሩን የሚወድ ትውልድ በማፍራት የጎላ ድርሻ ሲወጡ ቆይተዋል።
ተቋማቱ ምዕመናንን በማስተማር ለሀገር ልማት ሚናቸዉን እንዲወጡ ማስቻላቸውንም ጠቅስዋል።
የኃይማኖት ተቋማቱ በአስተምህሮቶቻቸው የወንድማማችነት ትርክትን በማስረጽ በሰላም ግንባታ እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ተግባሩን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
ተቋማቱ የዜጎች አንድነት እንዲጎለብትና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ በኩል ሚናቸውን በበለጠ እንዲወጡም አመልክተዋል ።
የኃይማኖት ተቋማት ሰላምና አንድነትን በማስተማር ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ልማት ያላቸዉ አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ (ረ/ፕ) ናቸዉ።
ተቋማቱ ትውልድን መልካም ስብዕና በማስታጠቅ የተጣለባቸዉን አደራ ሲወጡ መቆየታቸዉንም አንስተዋል።
የኃይማኖት ተቋማቱ የመደጋገፍና የመተሳሰብ ባህልን በማዳበር የህዝቡ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲጠናከር ሲያደርጉት የነበረውን ተግባር ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ትውልድን በስነ ምግባር የማነጽና ሰላምና ፍቅር እንዲፀና የማድረግ ተግባራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
በመድረኩ የኃይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ የክልል፣ የዞን እና የከተማ አስተዳደር የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ተመሳሳይ መድረክም በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ ይገኛል ።