ቀጥታ፡

በክልሉ ከኃይማኖት ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት ፈጣን እድገት ለማስመዝገብ የተጀመረው ተግባር ይጠናከራል

ሆሳዕና፤ የካቲት 30 /2018(ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሰላምና ልማት ሥራዎች ከኃይማኖት ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት ፈጣን እድገት ለማስመዝገብ የተጀመረው ተግባር ይጠናከራል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

ሙስሊሙ ማህበረሰብ የረመዳን ወርን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመደጋገፍ ሊያሳልፈው ይገባል

በክልሉ "በመደመር መንግስት እይታ የኃይማኖት ተቋማት ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሀይማኖት አባቶችና ምዕመናን የተሳተፉበት ክልል አቀፍ የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የክልሉ መንግስት ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል በማሳተፍ እያከናወናቸው ያሉ ሁሉን አቀፍ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ውጤታማ ናቸው።

ከኃይማኖት ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት ሰላምን ለማስቀጠልና ፈጣን እድገትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ተግባር ይጠናከራል ብለዋል፡፡

የኃይማኖት ተቋማት በክልሉ መንግሥት የተጀመሩ የሰላም ግንባታና የልማት ሥራዎችን በመደገፍ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንና ይህንንም ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

መንግስትና የኃይማኖት ተቋማት የሚመሩባቸው የራሳቸው ሥርአት እንዳሏቸው ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ለሀገረ  መንግሥት ግንባታ መጠናከር የተቋማቱ በትብብር መስራት ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

የሃይማኖት ተቋማት ከልማት ተሳትፏቸው ባለፈ የማህበረሰቡን አብሮነት በማጠናከር ለክልሉ ፈጣን እድገት የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡


 

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ በበኩላቸው፤ ለህዝቦች ሰላም፣ አብሮነት መጠናከርና በስነ ምግባር የታነፁ ዜጎችን ለማፍራት የሀይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

የሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚጠናከረው በትውልድ ቅብብሎሽ እንደሆነ ጠቁመው፣ ለዚህም ስኬት የኃይማኖት ተቋማት ብዝሃነትን ያከበረ መልካም ዜጋን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል።

በክልሉ ሰላምና የህዝቦች አብሮነትን በማጎልበት የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ከግብ እንዲደርሱ የሃይማኖት ተቋማት ያላቸውን ሚና እንዲያሳድጉም አስገንዝበዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ በየደረጃው ያሉ የክልሉ አመራሮች፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሁሉም መዋቅር የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና ምዕመናን ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም