ቀጥታ፡

ሙስሊሙ ማህበረሰብ የረመዳን ወርን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመደጋገፍ ሊያሳልፈው ይገባል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2018(ኢዜአ)፦ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የረመዳን ወርን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመደጋገፍ ሊያሳልፈው እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ገለጹ፡፡

“ነጃሺ ለሀገር” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው 6ኛው ታላቁ የጎዳና ላይ የኢፍጣር መርሃ-ግብር በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ዑስታዞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና የእስልምና እምነት ተከታዮች ተገኝተዋል።


 

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በመርሃ-ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ታላቁን የጎዳና ላይ ኢፍጣር በዚህ መልኩ በጋራ ማከናወን መቻሉ እጅግ የሚያስደስት ነው ብለዋል፡፡

ይህ መድረክ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አንድነት ከቃል ባለፈ በተግባር የታየበት መሆኑ ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች ኃላፊነቱን ወስደው መርሃ-ግብሩን ማዘጋጀታቸው የሚደነቅ ነው ያሉት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ወጣቶች ለአንድ ዓላማ ቆመው በማየቴ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።


 

ረመዳን የተቸገሩ ወገኖች የሚረዱበት ወር መሆኑን አስታውሰው ምዕመኑ በረመዳን ወር ማዕድ በማጋራት ችግረኞችን መደገፍ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሸይኽ መሐመድ ሸሪፍ ሃሰን በበኩላቸው፤ በረመዳን አብሮነትንና መረዳዳትን ማጎልበት ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም