በጋምቤላ ክልል የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ጋምቤላ ፤ የካቲት 30 /2018(ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።
በክልሉ ኮንትሮባንድ እና ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በመከላከል ጤናማ የገበያ ሥርአት ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቷል
በክልሉ በዘንድሮው ዓመት እየተካሄደ ባለው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች የማጠናከሪያ መርሃ ግብር በጎግ ወረዳ እየተካሔደ ነው።
ርዕሰ መስተዳደሯ አለሚቱ ኡሞድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፤የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጎላ ድርሻ አላቸው።
ይህን ታሳቢ በማድረግ በተራቆቱ አካባቢዎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በማጠናከር በክልሉ የተጀመረውን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ በትኩረት መስራቱ ይቀጥላል ብለዋል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማትና የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የአካባቢ መራቆትንና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል በኩል እመርታዊ ለውጥ እንዲመጣ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የተጀመረው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት ይገባዋል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ከተረጂነት ለመላቀቅ ለተቀመጠው ግብ መሳካት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች የላቀ አበርክቶ አላቸው።
ባለፉት አመታት ለተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች በተሰጠው ትኩረት የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙና የግብርና ምርታማነት እንዲጨምር ማስቻሉን ተናግረዋል።
በመሆኑም የተፈጥሮ ሃብትን መሠረት ያደረገ የግብርና ልማትን ለማስፋት የተጀመረው ጥረት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የጋምቤላ ክልልም ለግብርና ልማት የተመቸ ስነ ምህዳር ያለው አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ሃብት በአግባቡ አልምቶ ከመጠቀም አንፃር የቅንጅት ስራዎች እንደሚጠናከሩ ገልፀዋል።
በክልሉ ሲከናወን በቆየው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ የአፈር እርጥበታማነትንና ለምነትን በማሻሻል የሰብል ምርታማነትን እያሳደገ ይገኛል ያሉት ደግሞ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድሮው ቱት ናቸው።
በክልሉ የተፋሰስ ልማትን በማጠናከር የከርሰ ምድርና የገፀ ምድርን የውሃ ሀብት በማሻሻል የግብርና ልማቱን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በክልሉ በዘንድሮዉ የተፋሰስ ልማት ስራ በሁሉም ወረዳዎች በ101 ተፋሰሶች፤ 64 ሺህ ሄክታር የተራቆተ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል ።