በክልሉ ኮንትሮባንድ እና ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በመከላከል ጤናማ የገበያ ሥርአት ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ኮንትሮባንድ እና ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በመከላከል ጤናማ የገበያ ሥርአት ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቷል
አርባ ምንጭ ፤የካቲት 29/2018 (ኢዜአ):-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንትሮባንድ እና ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በመከላከል ጤናማ የገበያ ሥርአት ለመፍጠር ትኩረት መሰጠቱን ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
የክልሉ ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ-ሃይል የግማሽ ዓመት ሥራ አፈጻጸም ግምገማ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት በክልሉ ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድን በመከላከል ጤናማ የገበያ ሥርአት ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በገቢና ወጪ ንግድ ሥራ ላይ ሰፊ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸዋል።
ይሁንና ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች በኢኮኖሚው ውስጥ ጤናማ ግብይት እንዳይካሄድ ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ ነዳጅን ጨምሮ በድጎማ የሚመጡ ሸቀጦችን ህዝቡ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዳይጠቀም ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ ብለዋል።
እንደ አቶ ጥላሁን ገለጻ ጥራትና ብቃቱ ያልተረጋገጠ ህገወጥ ምርት ለማህበራዊ ቀውስ ከመዳረግ ባለፈ የተለያዩ ግጭቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ ፖለቲካዊ ቀውስ ያስከትላል።
በክልሉ የተቋቋመው የኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ-ሃይል የተቀናጀ ቁጥጥር በማድረግ ጤናማና ፍትሃዊ የንግድ ሥርአት እንዲኖር ሃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በበኩላቸው እንዳሉት በግማሽ ዓመቱ ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ መቆጣጠርን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች ውጤት ተመዝግቧል።
ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የህግ የበላይነትን በመሸርሸርና ገበያን በማዛባት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ስለሚያስከትል የመከላከል ሥራው በቅንጅት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት የኑሮ ውድነት ለመፍጠር በሸቀጦችና ሌሎች ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 21ሺህ 600 የንግድ ድርጅቶች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱንም ተናግረዋል።
ከነዳጅ ጋር በተያያዘ ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው ነዳጅ በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ መያዙን የገለጹት ወይዘሮ ሰናይት፣ በነዳጅ ግብይት ህግ በተላለፉ 15 ማደያዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
ግብረ-ሃይሉ ባደረገው ቁጥጥርም ከ910 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም 28 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ መድሃኒትና ምግቦችን በመያዝ በህዝብ ላይ ሊደርስ የነበረን የጤና ችግር መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል።
በመድረኩ የክልል፣ የዞኖችና የከተሞች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና የፀጥታ አካላት የተሳተፉ ሲሆን በቀረበው ሪፖርት ላይም ውይይት ተደርጓል።