የአየር ጤና - ካራ ወለቴ እና የአውቶብስ ተራ - መሳለሚያ 18 ማዞሪያ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተፋጠነ ሁኔታ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ጤና - ካራ ወለቴ እና የአውቶብስ ተራ - መሳለሚያ 18 ማዞሪያ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተፋጠነ ሁኔታ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2018 (ኢዜአ)፦የአየር ጤና - ካራ ወለቴ እና የአውቶብስ ተራ - መሳለሚያ 18 ማዞሪያ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተፋጠነ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ባለሀብቶችን በቀጥታ ማሳተፍ የሚያስችል ዘመናዊ የገበያ ስርዓት ተፈጥሯል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአየር ጤና - ካራ ወለቴ እና አውቶብስ ተራ - መሳለሚያ -18 ማዞሪያ የመንገድ ፕሮጀክቶችን የሥራ ሂደት ጎበኝተዋል።
የአየር ጤና - ካራ ወለቴ የመንገድ ፕሮጀክት በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም አውቶብስ ተራ - መሳለሚያ - 18 ማዞሪያ የመንገድ ፕሮጀክት በመጪው ታህሳስ ወር ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከንቲባዋ በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለጹት፤ አውቶብስ ተራ - መሳለሚያ - 18 ማዞሪያ መንገድ ግንባታ ለረጅም ጊዜያት በተለያዩ እክሎች ምክንያት ተጓቶ የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን በተቀናጀና በፈጣን ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ 3 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ባለ 6 መስመር መንገድ እንደሆነ ገልፀዋል።
ዘመናዊ የመሿለኪያ መንገድ underpass የሚያካትት ሲሆን ሁሉም የፍሳሽ፣ የኤሌክትሪክና የውሃ መሠረተ ልማቶች በተቀናጀ መልኩ የተሟሉለት ነው ብለዋል።
ይህ የመንገድ ፕሮጀክት በመጪው ታህሳስ ወር ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተያያዘም ከንቲባዋ የአየር ጤና - ካራ ወለቴ የመንገድ ፕሮጀክት የሥራ እንቅስቃሴን የጎበኙ ሲሆን ፕሮጀክቱ በተሻለ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
ይህ ፕሮጀክት 5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን የጎን ስፋቱ ደግሞ 40 ሜትር እንደሆነና ይህም የአካባቢውን የትራፊክ ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያቃልል ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ግንባታው በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንዳለ አንስተው በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአካባቢው የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስና ለከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ መሳለጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል ብለዋል።
በአጠቃላይ በከተማዋ 140 የመንገድ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ተናግረው 104 የሚሆኑት በከተማው መንገዶች ባለሥልጣን በራስ አቅም እንዲሁም ቀሪዎቹ በግል ኮንትራክተሮች እየተገነቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሙህዲን ረሻድ፤ መንገዶቹ በከተማዋ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ በፍጥነት እና በጥራት እንዲጠናቀቁ ድጋፍ እና ከትትል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።