ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ባለሀብቶችን በቀጥታ ማሳተፍ የሚያስችል ዘመናዊ የገበያ ስርዓት ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ባለሀብቶችን በማንኛውም ጊዜና ቦታ በቀጥታ ለማሳተፍ የሚያስችል ዘመናዊ የገበያ ስርዓት መፈጠሩን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥራ አስፈጸሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ገለፁ።

የኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ “ንዋይ” የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያን ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ (ESX) የካፒታል ገበያን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል “ንዋይ” የተሰኘ የሞባይል ግብይት መተግበሪያ ዛሬ ይፋ አድርጓል።


 

ይህ መተግበሪያ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ማንኛውም ግለሰብ በእጁ ላይ ያለውን የሞባይል ስልክ በመጠቀም፣ በአክሲዮን እና የዕዳ ሰነዶች ግብይት ውስጥ በቀጥታ ለመሳተፍ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥራ አስፈጸሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በመተግበሪያው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ እንደተናገሩት፣ መተግበሪያው ሁሉም ዜጋ በአቅሙ ልክ የሚሳተፍበትን ምቹ እና ዘመናዊ የገበያ ዕድል ፈጥሯል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ወደ ሥራ የገቡት የቴሌ ብር እና የሲቢኢ (CBE) መተግበሪያዎች ያስመዘገቡት ስኬት ለዚህ መተግበሪያ ውጤታማነት እንደ ማሳያ እንደሚጠቀስም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ አዲሱ መተግበሪያ ገበያውን በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እጅ ተደራሽ ያደርገዋል።


 

በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ባለሀብቶችም በማንኛውም ጊዜና ቦታ በቀጥታ እንዲሳተፉ እድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

በተጨማሪም መተግበሪያው የሰነድ ግዢና ሽያጭ ትዕዛዞችን በስልክ ማስተላለፍና መፈጸም እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በቀጣይ ኢንቨስተሮች ለገበያው ያላቸውን ልምድ እንዲያዳብሩ የአገናኝ አካላት ጥረት ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተህልቁ በበኩላቸው፤ በርካታ ሀገራት ወደዚህ ዓይነት የቴክኖሎጂ ሥርዓት ለመድረስ ረጅም ጊዜ እንደወሰደባቸው አስታውሰዋል። 


 

ኢትዮጵያ ግን ካለፈው ተሞክሮ በመማር በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመናዊ የገበያ ሥርዓት ማበጀቷን ገልጸዋል።

ለዚህም ስኬት መንግስት ህጎችን ግልፅና ተገማች ማድረጉ እንዲሁም ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ይህን የገበያ ሥርዓት ልዩ የሚያደርገው አካታችነቱ በመሆኑ፣ በሁሉም የሀገሪቱ ጫፍ ያሉ ዜጎች ተሳታፊ እንዲሆኑና የኢንቨስትመንት አካውንት በመክፈት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል።

መተግበሪያው በአሁኑ ወቅት በአንድሮይድ (Android) እና በአይኦኤስ (iOS) ስልኮች ላይ ለመጫን ዝግጁ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የካፒታል ገበያ ባለቤት ለማድረግ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም