አብን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ ይገኛል- በለጠ ሞላ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
አብን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ ይገኛል- በለጠ ሞላ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ የካቲት 30 /2018(ኢዜአ)፦የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችለውን ዝግጅት እያከናወነ እንደሚገኝ የአብን ሊቀመንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለጠንካራ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ በቅንጅት እየተሠራ ነው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሃ ግብር መሠረት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
በምርጫ ቦርድ እውቅና የተሰጣችው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክቶቻቸውንና ማኒፌስቶዎቻቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ዕጩዎቻቸውን በማስመዝገብ የምርጫ ክርክር እያካሄዱ ነው።
በተጨማሪም ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ ሂደት በይፋ ተጀምሯል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ አብን ካለፈባቸው በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ወጥቶ አሁን ላይ ራሱን ለውድድር እያዘጋጀ ይገኛል።
አብን በምርጫው ለመሳተፍ የሚያደርገው ጥረት በአማራ ክልል ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎች ጭምር ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በመሆኑም ፓርቲው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ደጋፊዎቹን በማስተባበርና ድርጅታዊ መዋቅሩን በማጠናከር በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤታማ ለመሆን በትኩረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ምርጫው ስኬታማና ተዓማኒ እንዲሆን መንግሥት፣ ሕዝቡና የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራና በቅንጅት በመስራት የሚጠበቅባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም መንግሥት ሁሉም ፓርቲዎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት ምቹና አስተማማኝ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠሩን እንዲያጠናክር አንስተዋል።
መገናኛ ብዙኃንም ለሁሉም ተፎካካሪ ኃይሎች እኩልና ፍትሐዊ የሆኑ የብሮድካስት መድረኮችን በማመቻቸት የድርሻቸውን ሊያበረክቱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
እነዚህ የተቀናጁ ጥረቶች ኢትዮጵያ ወደ ላቀ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንድትሸጋገር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖራቸውም ሊቀመንበሩ አብራርተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሐሳብ ልዕልናን በማስቀደም ተጨባጭና ለሀገር የሚጠቅሙ አማራጭ ዕቅዶቻቸውን ለመራጩ ሕዝብ ማቅረብ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ፓርቲያቸው አሁን ላይ የተፈጠሩትን የፖለቲካ ዕድሎች በአግባቡ በመጠቀም፣ ሂደቱ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ድርጅታዊ ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።