ቀጥታ፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለጠንካራ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ በቅንጅት እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2018 (ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለጠንካራ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ።

ይህ የተባለው "የዴሞክራሲ ባህልን በምርጫ መገንባት" በሚል ርዕስ በተዘጋጀ የፓናል ውይይት ላይ ነው።

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባን ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል

የፓናል ውይይቱ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ያለው 5ኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት አካል ሲሆን፥ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።


 

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ እንደገለጹት፥ ምርጫ የአንድ ወቅት ተግባር ቢሆንም ሂደቱና ከምርጫው በኋላ የሚከናወኑ ተግባራት ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ናቸው። 

የምርጫ ሂደቱ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት፣ መቻቻልና መግባባት የሰፈነበት እንዲሆን የተጀመሩ ቅንጅታዊ አሠራሮች መጠናከር እንዳለባቸው አስረድተዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚኖረውን አዎንታዊ ሚና ማጉላት እንደሚገባ ጠቅሰው፥ ለዚህም በተቋማት መካከል የተናበበ ሥራ ወሳኝ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ንዋይ በበኩላቸው፥ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ሰፋፊ የዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።


 

የምርጫ መርኃ ግብሩ በጊዜ ሰሌዳው መሠረት እንዲፈጸም ቦርዱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት የእጩዎች ምዝገባ ተደራሽነትን ባረጋገጠ መልኩ መጠናቀቁንና ለመራጮች ምዝገባም የተለያዩ አማራጮች መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሀሳቦቻቸውን በመገናኛ ብዙኃን የሚያስተዋውቁበት ምቹ የሥራ ምኅዳር መፈጠሩን በማንሳት፥ ይህም የዴሞክራሲ ባህል እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንዳሉት፤ በምርጫው ሂደት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በትኩረት እየተሠራ ነው።

ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ድርጅቶቹ ያላቸውን ሚና እንዲያጎለብቱ የተለያዩ ሥርዓቶች መዘርጋታቸውን በመግለፅ፥ ባለሥልጣኑ ለዚህ የሚረዳ ራሱን የቻለ ዕቅድ አውጥቶ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አሕመድ ሁሴን በበኩላቸው፥ ሕዝቡ በምርጫው ላይ በንቃት እንዲሳተፍ  ለማስገንዘብ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል። 

ምርጫ ዜጎች ተወካዮቻቸውንና መሪዎቻቸውን በድምፃቸው በመምረጥ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን እውን መሆን የሚያረጋግጥና ለሀገር ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሕብረት ለምርጫ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበራ ኃይለማርያም፥ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የታዛቢዎችን ቁጥር በላቀ ሁኔታ ከፍ ለማድረግ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

በተለይም የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውንና ሂደቱ ፍትሐዊና ተአማኒ እንዲሆን የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ላይ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም