በምርጫ ካርዳችን የነገዋን ኢትዮጵያ ለማጽናት ተዘጋጅተናል- ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫ ካርዳችን የነገዋን ኢትዮጵያ ለማጽናት ተዘጋጅተናል- ነዋሪዎች
ወላይታ ሶዶ ፤ የካቲት 28/2018 (ኢዜአ)፦በምርጫ ካርዳችን የሚበጀንን በመምረጥ የነገዋን ኢትዮጵያ ለማጽናት ተዘጋጅተናል ሲሉ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለጠንካራ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ በቅንጅት እየተሠራ ነው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ዛሬ የመራጮች ምዝገባ መጀመሩ ይታወቃል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ፤ በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ተሳትፈን ዲሞክራሲያዊ መብታችንን ለመጠቀምና የነገዋን ኢትዮጵያ ለማጽናት የመራጭነት ካርድ ወስደናል ብለዋል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ዘሪሁን ሎሪሶ፤ በምርጫው ሂደት የአንድ ሰው ድምጽ ትልቅ ድርሻ እንዳለው በመረዳት በመራጭነት መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ምርጫው በቀጣይ ሀገሪቱን የሚመራ ፓርቲን ወደ ስልጣን ለማምጣት ብቸኛ መንገድ በመሆኑ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀምና የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት መወሰናቸውን ነው የተናገሩት።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በመገናኛ ብዙሃን እያካሔዱ ባለው የክርክር መድረክ ፕሮግራማቸውንና ማኒፌስቷቸውን እያስተዋወቁን በመሆኑ የሚበጀንን ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ወስደናል ነው ያሉት።
ወይዘሮ የኔዓለም ሳሙኤል በበኩላቸው፤ የምፈልገውን ፓርቲ ወደ ስልጣን ለማምጣት የመራጭነት ካርድ መውሰድ የግድ በመሆኑ ወደ ምርጫ ጣቢያው በመምጣት ተመዝግቤ ካርድ ወስጃለሁ ብለዋል።
ምርጫው ፍትሐዊ፣ ሰላማዊና ቅቡልነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻችንን ለመወጣትና ለሚበጀን የፖለቲካ ፓርቲ ድምፃችንን ለመስጠት ተዘጋጅተናል ሲሉም ተናግረዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አማኑኤል ፊሊጶስ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በመገናኛ ብዙሃን የሚደረጉ ክርክሮች የተሻለ አማራጭ ያለው የፖለቲካ ፓርቲን ለመለየት የሚያስችል ነው ብለዋል።
በመሆኑም የነገዋን ኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል በምርጫ ካርዳቸው ለመወሰን በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።