ቀጥታ፡

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባን ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27 /2018(ኢዜአ)፦ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ ገለጹ። 

47 የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎች ማስመዝገባቸውንም ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ ሰባተኛውን ጠቅላላ  ምርጫ ለማካሄድ በተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ  ሰጥተዋል። 

በመግለጫቸውም የመራጮች ምዝገባ ከነገ ጀምሮ ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የመራጮች ምዝገባ ለአንድ ወር እንደሚካሄድ ገልጸው፤ ምዝገባው በዲጂታል እና በማንዋል መልኩ እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።

ከፕሌይ ስቶርና አፕ ስቶር "ምርጫዬ" የተሰኘውን መተግበሪያ አውርደው በስልካቸው መመዝገብ የሚችሉ ዜጎች በራሳቸው መመዝገብ እንደሚችሉም ጠቁመዋል። 

በአካል ምርጫ ጣቢያዎች የሚመዘገቡ መራጮችን ለማስተናገድም ቦርዱ ለምርጫ አስፈጻሚዎች ታብሌቶችን ማሰራጨቱን አብራርተዋል።  

ከ3 ጂ በላይ ኢንተርኔት ተደራሽነት ባለባቸው አካበቢዎች የመራጮች ምዝገባው በዲጂታል እንደሚደረግ ጠቁመው፤ ለዚህም ቦርዱ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል። 

በሌላ በኩል ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን ማስመዝገባቸውን አክለዋል። 

ከዚህ ውስጥ 2ሺህ 198 ዕጩዎች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመዘገቡ ሲሆን 8 ሺህ 736 ለክልል ምክር ቤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።  

የቦርዱ ሰብሳቢ እንዳሉት 73 በግል በዕጩነት የቀረቡ ሲሆን ከዚሁ ውስጥ 69ኙ ወንድ 4ቱ ደግሞ ሴት ዕጩዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። 

ቦርዱ ፓርቲዎች የሚወዳደሩበትን ምልክት ይፋ ያደረገ ሲሆን የዕጩዎች የስነ ምግባር ደንብንም ፓርቲዎች እንዲፈርሙ መደረጉን ከቅድመ ዝግጅት ስራዎች መካከል መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም