የእንስሳት ምርት ጥራትና ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች እየተዘረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የእንስሳት ምርት ጥራትና ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች እየተዘረጉ ነው
አዳማ፤ የካቲት 28/2018 (ኢዜአ)፦ የእንስሳት ምርት ጥራትና ደህንነትን በዘላቂነት ለመጠበቅና የዘርፉን አሰራር ለማዘመን የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን እየዘረጋ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ገለጸ።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የኢትዮጵያን የንግድ ምህዳር ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ታላቅ ዕድል ነው
ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የረቂቅ ደንቡን ይዘት በባለድርሻ አካላት ግብዓት ለማዳበር ያለመ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የእንስሳት ምርት ጥራትና ደህንነትን በህግ ለመደገፍ አዋጅ ቁጥር 1376/2018 ወጥቶ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል።
ይህም የሀገሪቱን የእንስሳትና የእንስሳት ውጤቶች የንግድ እንቅስቃሴ ለማሳለጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው አሰራር ለመዘርጋት ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
አምባሳደር ድሪባ አክለውም፤ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና ምርቱን የሚረከቡ ሀገራት የሚቀበሏቸው የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
አሁን ላይ በእፅዋትና በእንስሳት ዘርፎች አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና ስታንዳርዶች ፀድቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
የህግ ማዕቀፎቹ የዘርፉ ኢንዱስትሪዎች፣ በተለይም የስጋ አምራቾች ፍላጎትን መሰረት ያደረጉና ከዓለም አቀፍ አሰራር ጋር የተናበቡ እንዲሆኑ ታስቦ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የባለሥልጣኑ የሬጉላቶሪ ዘርፍ ዳይሬክተር ሃሚድ ጀማል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ባለፉት ሰባት ወራት የእንስሳት ምርት ለማምረት ፈቃድ የተሰጣቸውን ተቋማት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የአሰራር ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ምርት ወደ ውጭ ከመላኩ በፊት ከማምረቻው ጀምሮ ጥራትና ደህንነቱ መጠበቅ እንዳለበት ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፤ ምርት በቁምም ሆነ ታርዶ ለተጠቃሚው ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ እንዲላክ ተቋሙ ከግብርና ሚኒስቴርና ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የባለሥልጣኑ የእንስሳት ምርት ሬጉላቶሪ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አያሌው ሹመት በበኩላቸው፤ የህግ ማዕቀፎቹ የኤክስፖርት ዘርፉን ማነቆዎች የሚቀርፉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ይህም የቁም እንስሳት፣ ስጋ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ዓሣ፣ ወተትና የማር ምርቶችን የቁጥጥር አሰራር የሚያዘምን መሆኑን ጠቅሰዋል።
በህግ ማዕቀፎቹ ዝግጅት ወቅት የዓለም ንግድ ድርጅትን ጨምሮ የናሚቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ቦትስዋና፣ እንግሊዝና የብራዚል ምርጥ ተሞክሮዎች እንዲካተቱ አድርገናል ሲሉም ገልጸዋል።
የህግ ማዕቀፎቹ ተግባራዊ መሆን ለሀገሪቱ የወጭ ንግድ ውጤታማነት የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም ተመላክቷል።