የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የኢትዮጵያን የንግድ ምህዳር ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ታላቅ ዕድል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የኢትዮጵያን የንግድ ምህዳር ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ታላቅ ዕድል ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) የኢትዮጵያን የንግድ ምህዳር ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ታላቅ ዕድል ከመሆኑም ባለፈ ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን የንግድ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግር የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ ቀነኒሳ ለሚ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና መመስረት ለኢትዮጵያ ነጋዴዎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም ነጋዴዎች ምርታቸውን በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ያለ ታሪፍና የንግድ መሰናክል የመሸጥ ዕድል እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡
በህጋዊ ውድድር ውስጥ ማለፋቸው ነጋዴዎች ራሳቸውን ዘወትር እንዲያሻሽሉ ያደርጋል ያሉት ዋና ጸሐፊው አዳዲስ አሰራሮችን እንዲከተሉና ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ምቹ ዕድል እንደሚፈጠርም ገልጸዋል፡፡
የገበያው መከፈት ከሌሎች አፍሪካውያን ነጋዴዎች ጋር የንግድ ስልቶችን ለመቅሰም ትልቅ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱ የንግድ ህጎች ከአህጉራዊው ስርዓት ጋር መጣጣማቸው የውጭ ኢንቨስተሮችን ይስባል፤ ይህም ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ለሀገራዊ ብልጽግና መሰረት ይሆናል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዕቃ ንግድ ፕሮቶኮል ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከኬኒያና ከሶማሊያ ጋር የንግድ ልውውጥ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡
ይህም ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ጠቅሰዋል፡፡
ምክር ቤቱ ነጋዴዎች ያላቸውን ጸጋ ለይተው እንዲያውቁና በምርቶቻቸው ላይ እሴት በመጨመር በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ስልጠናና ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡