የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አስተማማኝ የግብርና ሥርዓት መገንባት ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አስተማማኝ የግብርና ሥርዓት መገንባት ይጠበቅባቸዋል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2018(ኢዜአ)፦የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አስተማማኝ የግብርና ሥርዓት መገንባት እንደሚጠበቅባቸው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ገለጸ።
"በምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም ግብርናን ማስፋፋት" በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ቀጣናዊ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በኢጋድ፣ የዓለም ባንክ የአፍሪካ ቢሮ፣ የሥርዓተ ምግብ ፕሮግራም ለምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ፣ የደቡባዊ አፍሪካ የግብርና ምርምርና ልማት ማስተባበሪያ ትብብር በተዘጋጀው መድረክም የግብርና ማሻሻያ ምክረ ሀሳቦችን እንደሚያፈልቅ ይጠበቃል።
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ተወካይ ዳህር ኤልሚ፤ በአየር ንብረትና በሥነ-ምኅዳር ደኅንነት የሚከሰት ለውጥ የግብርና ምርታማነት ላይ ጫና እያሳደረ ነው ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው የአፈር መራቆት፣ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ዝናብ እጥረትና በርሃማነት የምስራቅ አፍሪካ የግብርና ምርታማነትና የምግብ ፍጆታ ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድሩ ገልጸዋል።
በዚህም የቀጣናው ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አስተማማኝ የግብርና ሥርዓት ለመገንባት የቴክኖሎጂ፣ የግብዓትና የመረጃ ትንተና አቅም መገንባት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣንም የቀጣናውን ሀገራት የግብርና ምርታማነት የሚያሻሽል የአየር ሁኔታ የመረጃ ትንተና ተደራሽ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት የተፈጥሮ ሃብትና የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ፕሮግራም ዳይሬክተር አወቀ ሙሉዓለም በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ሥርዓት ውጤት እያስመዘገበ ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችም የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ የአርሶና አርብቶ አደሩን የግብርና ምርታማነት እያሳደገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዓለም ባንክ ከፍተኛ የግብርና ባለሙያ ቲም ሮበርትሰን፤ የግብርና ምርታማነት የሚያዘምኑ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማስፋት የቀጣናው ሀገራት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የኒውዝላንድ አምባሳደር የኢጋድና የአፍሪካ ሕብረት ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ኦሊቪያ ኦዌን በበኩላቸው፤ የግብርና ምርታማነትን ማረጋገጥ ለአፍሪካ ዕድገትና ብልጽግና ወሳኝ ነው ብለዋል።
የቀጣናውንና አፍሪካን የግብርና ሥርዓት ለማዘመን በሚደረገው ጥረትም የኒውዝላንድ መንግስትና የልማት አጋሮች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በፎረሙ ላይ የኢጋድ አባል ሀገራት ተወካዮች፣ ፖለሲ አውጪዎች፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮችና ተመራማሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።