ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች መራጮች የምርጫ ካርድ መውሰድ ጀምረዋል

ጭሮ፣ ነጌሌ ቦረና፤ የካቲት 28/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች መራጮች በየምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ካርድ መውሰድ ጀምረዋል።

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባን ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰሌዳ መሰረት የመራጮች ምዝገባ ዛሬ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሯል።

በጊዜ ሰሌዳው መሰረት የመራጮች ምዝገባ ከተጀመረባቸው የኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች መካከል ምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጭሮ፣ ምስራቅ ቦረና ነጌሌ፣ ምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተሞች ይጠቀሳሉ።

ኢዜአ በጭሮ ከተማ የምርጫ ካርድ ሲወስዱ ያገኛቸው ነዋሪዎች በምርጫው በንቃት ለመሳተፍ ቀድመው የምርጫ ካርድ በመውስድ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።


 

በከተማው የቡርቃ ጭሮ ቀበሌ ነዋሪ ከድር ሰይድ እንዳሉት፤ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሀገሪቱ የተያያዘችውን እድገትና ብልፅግና ከዳር ለሚያደርስ ተወዳዳሪ ድምፃቸውን ለመስጠት ተዘጋጅተዋል።

የዴሞክራሲ ስርዓት መሰረት የሚይዘው እና የሀገር ዕድገት የሚረጋገጠው በምርጫ በመሆኑ በንቃት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ይወክለኛል የሚሉትን ተወዳዳሪ ለመምረጥ መመዝገባቸውን የተናገሩት ደግሞ በከተማው ጨፌ አራራ ቀበሌ ነዋሪ መሐመድ ሐሰን ናቸው።

''ባለፉት አራት ተከታታይ ምርጫዎች ተሳትፌያለሁ'' የሚሉት አስተያየት ሰጪው የዘንድሮው ምርጫ የሀገሪቱን የዕድገት ጉዞ ለማፋጠን ወሳኝ በመሆኑ በትኩረትና በንቃት ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ መብቱን ተጠቅሞ ቀድሞ በመመዝገብ ለሚፈልገው አካል ድምፁን ሊሰጥ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በምስራቅ ቦረና ዞን የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪ ወይዘሪት ገሊላ ፍቃዱ፤ በነገሌ ምርጫ ክልል ከሀሎ ጋፍትሮ ምርጫ ጣቢያ የመራጭነት ካርድ ወስደዋል፡፡


 

ካርድ የወሰዱት በመጪው ግንቦት ወር በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ለአብሮነት፣ ለሰላም፣ ለልማትና ለሀገራዊ እድገት ይሰራል ለምትለው ፓርቲና እጩ ተወዳዳሪ ድምጽ ለመስጠት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሁሉም የምርጫ ካርድ በመውሰድ በሀገራዊ ምርጫው በመሳተፍ ለሚፈልገው ፓርቲ ድምጹን እንዲሰጥም መክረዋል፡፡

በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ ቡርቃ ጃቶ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ፈይሳ ጭምዴሳ፣ በጠቅላላ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።


 

ሌሎችም ሀገርንና ህዝብን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ የፖለቲካ ፓርቲ መምረጥ እንዲችሉ በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ካርድ እንዲወስዱም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም