ሙዚየሙ ለሀገር ግንባታ ዝግጁ የሆነ ትውልድ ለመቅረጽ ትልቅ ፋይዳ አለው - ኢዜአ አማርኛ
ሙዚየሙ ለሀገር ግንባታ ዝግጁ የሆነ ትውልድ ለመቅረጽ ትልቅ ፋይዳ አለው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሙዚየም የዘመናት የጀግንነት ጉዞ የሚዘክር ሕያው አሻራ ከመሆን ባለፈ ለሀገር ግንባታ ዝግጁ የሆነ ትውልድ ለመቅረጽ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የመከላከያ ሙዚየምና ቅርስ ጥናት አስተዳደር ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ጥሩዬ አሰፌ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ በፈተናዎች ጸንታ የቆመችው በማይበገረው የሠራዊታችን ተጋድሎ ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሀገሪቱን ታሪካዊ ወታደራዊ ጉዞና የጀግንነት አሻራዎችን የያዘውን የኢትዮጵያ ሰራዊት ሙዚየም ጎብኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ጉብኝቱን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሙዚየም የጀግንነታችን ማኅደር፣ የልዕልናችን ምስክር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ በፈተናዎች ጸንታ የቆመችው በማይበገረው የሠራዊታችን ተጋድሎ እንደሆነም ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጃንሜዳ አካባቢ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሠራዊት ሙዝየም መጎብኘታቸውን ገልጸው፤ በሙዝየሙ የዘመናት የጀግንነት ጉዞ የሚመሰክሩ ህያው አሻራዎችን መመልከታቸውን ጠቁመዋል።
የመከላከያ ሙዚየምና ቅርስ ጥናት አስተዳደር ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ጥሩዬ አሰፌ እንደገለጹት፤ ሙዚየሙ ከአክሱም ዘመነ መንግስት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያሉ የኢትዮጵያን ወታደራዊ ታሪኮች እና ቅርሶች በዝርዝር ሰንዶ የያዘ ነው።
ከለውጡ በኋላ መንግስት ለታሪክና ለቅርስ ባሳየው ቁርጠኝነት ሙዚየሙ በዘመናዊ መልኩ እንደ አዲስ መገንባቱን ጠቅሰው የኢትዮጵያ ሠራዊት ጀግንነት በተግባር የሚታይበት ነው ብለዋል፡፡
ጀግኖች አባቶቻችን በዓድዋ ጦርነት ወቅት የተጠቀሙባቸው መሣሪያዎችን ጨምሮ የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር የተከፈሉ መስዋዕትነቶችን የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች እንደሚገኙበትም አስረድተዋል።
የሙዚየሙ መገንባት ትውልዱ የሀገሩን ታሪክ በቀላሉ እንዲረዳ ያስችለዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ሙዚየሙ ሠራዊቱን በጀግንነት የሚያነሳሳ ከመሆኑ ባለፈ ወቅቱ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት በመክፈል ለሀገር ግንባታ ዝግጁ የሆነ ትውልድ ለመቅረጽ ያስችላል ብለዋል።
ሙዚየሙ ኢትዮጵያ በታሪኳ ሁሉ ሉዓላዊነቷን በተግባር ማረጋገጧን በግልጽ የሚያሳይ እንደሆነም ጨምረው አንስተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በቦታው ተገኝተው መጎብኘታቸውም ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባቸው ጠቁመው ለሙዚየሙ ታሪካዊ ፋይዳ እውቅና የሚሰጥና ለዘርፉ የተሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያረጋግጥ መሆኑንም ተናግረዋል።