ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ በፈተናዎች ጸንታ የቆመችው በማይበገረው የሠራዊታችን ተጋድሎ ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27 /2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በታሪኳ በፈተናዎች ጸንታ የቆመችው በማይበገረው የሠራዊታችን ተጋድሎ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የኢትዮጵያ ሠራዊት ሙዚየም የጀግንነታችን ማኅደር፣ የልዕልናችን ምስክር ነው ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ በታሪኳ በፈተናዎች ጸንታ የቆመችው በማይበገረው የሠራዊታችን ተጋድሎ እንደሆነም ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በጃንሜዳ አካባቢ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሠራዊት ሙዝየም መጎብኘታቸውን ገልጸው፤ በሙዝየሙ የዘመናት የጀግንነት ጉዞ የሚመሰክሩ ህያው አሻራዎችን መመልከታቸውን ጠቁመዋል።

ከ1950ዎቹ ጀምሮ እንዲቋቋም ሲታለም የቆየው ይህ የጦር መዝየም፣ በፖለቲካዊ ውሳኔዎች ብቅ እልም ሲል ቆይቶ ዛሬ በለውጡ መንግሥት ቁርጠኝነት ተቋማዊ ቁመና ተላብሶ እውን መሆኑን ነው ያነሱት።

ይህ ስኬት ለሚገነባው ግዙፍ ብሔራዊ የሠራዊት ሙዝየምም እንደ ማዕዘን ድንጋይ የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዓድዋ ዘመን በፊት የነበሩ ብርቅዬ መሣሪያዎችና የነገሥታቱ ትጥቆችን ጨምሮ በሙዚየሙ ያሉት የጦር ታሪክና ቅርሶች የጀግኖቻችንን ታሪክ የሚዘክሩ ናቸው ብለዋል።


 

ከ1900 ጀምሮ ያለውን ዘመናዊ የተቋም ግንባታ፣ የጦር መሣሪያዎች ዝግመተ ለውጥና መከላከያችን የደረሰበትን አስደናቂ የምህንድስና ጉዞ የሚያስቃኘው ይህ ማዕከል፤ ለሠራዊቱና ለትውልድ ታሪክን፣ ዕውቀትንና መነሳሳትን የሚያስታጥቅ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።

በሙዝየሙ፣ ከትናንቱ እንማርበታለን፤ ዛሬን እንገመግምበታለን፤ ለነገ ደግሞ እናቅድበታለን። አፍሪካውያንና መላው በፀረ ቅኝ አገዛዝ የታገለ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ይሄንን ሙዝየም በመመልከት የራሱን ታሪክ እንዲያደንቅ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብዣ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሠራዊት የታሪካችን ኩራት፣ ከሀገር አልፎም በዓለም ስሙ ከፍ ብሎ የሚነሳ የሰላም ዘብ ነው ብለዋል።


 

የታሪካችን ድምቀት የሆነው የሠራዊታችን ገድል ለትውልድ እንዲሸጋገር በዘመናዊ መንገድ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ይበል የሚያሰኙ በመሆናቸው፤ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል ሱሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም