ቀጥታ፡

ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የድርሻችንን እንወጣለን- የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች

ቦንጋ፤ የካቲት 28/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምና አንድነትን የሚያመጣ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለፁ። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የአገረ መንግሥት ግንባታን ለማጽናት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል

በሀገሪቱ ስር የሰደዱ አለመግባባቶችና ልዩነቶች አካታችና አሳታፊ በሆነ መንገድ ለመፍታት፣ ዘላቂ ስላምንና አንድነትን ለማምጣት እንዲቻል የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እየተሰራ ነው።

ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት የአጀንዳ ልየታ ስራውን በማጠናቀቅ ወደ ዋናው ምክክር የሚያስገቡ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የቦንጋ ከተማ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፤ ምክክሩ በኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባትና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ፋይዳው የላቀ በመሆኑ ለስኬታማነቱ እንሰራለን ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባት የሆኑት መጋቤ ሀይማኖት እሸቱ በላይ ፤ በመመካከርና ተቀራርቦ በመነጋገር የማይፈታ ችግር፣ የማንሻገረው ፈተና ባለመኖሩ የሰላምን መንገድ መከተል ይገባል ብለዋል።


 

የምክክር ኮሚሽኑ መቋቋም በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩና ስር የሰደዱ ቅራኔዎችና አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ኢትዮጵያን በልማት ቀዳሚ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚህም የኮሚሽኑን ስራ መደገፍና የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ በመሆኑ  የድርሻቸውን እንደሚወጡ አመልክተዋል።

የካፋ ዞን የወንጌል አማኞች ካውንስል ዋና ፀሐፊ ፓስተር መለሰ እንዳለ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች ተፈተው ዜጎች የተረጋጋና ምቹ ሕይወት እንዲመሩ ሰፊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።


 

በምክክሩ ያሉብንን ልዩነቶች ተቀራርበን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት ሰላሟ የተረጋገጠና የበለፀገች ሀገርን ለትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

ለዘመናት የዘለቁ አለመግባባቶችን ተመካክሮ በመፍታት መተማመን መፍጠር ይቻላል ያሉት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ ኡስታዝ ሸረፈዲን ኑሩ ናቸው።


 

ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸውን ተግባራት መደገፍም ሰላምና አንድነትን የሚያመጣ በመሆኑ የሐይማኖት ተቋማት ዋነኛ ተግባራችን አድርገን የምንሔድበት ተልዕኮ ነው ብለዋል።

በሀገሪቱ አሳታፊና አካታች ምክክር የማድረግ ልምድ ባለመኖሩ መሰረታዊ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ሲፈጠሩ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት አዳጋች እንደነበር ያስታውሱት ደግሞ  የሀገር ሽማግሌ አቶ ወርቁ  ወልደማርያም ናቸው።


 

በአሁኑ ወቅትም ማሕበረሰቡ የምክክር ኮሚሽኑ በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ለማድረግ የሚጠበቅብኝን ሚና ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብለዋል።

የሀገር ሽማግሌና የካፋ ባህል ምክር ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ በየነ በቀለ በበኩላቸው፤ ምክክሩ ለዘመናት ሀገራችንን ወደ ኋላ ሲጎትቱ የቆዩ ችግሮችን በጋራ ተነጋግሮ በመፍታት ወደ ፊት ለመራመድ  የሚያስችለንን እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።


 

ኮሚሽኑ በሁሉም አካባቢዎች ያለምንም ልዩነት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ባሳተፈና ባካተተ መልኩ ውይይቶችን ሲያካሄድ መቆየቱ የራሳችንን ችግር በራሳችን ለመፍታት እንደምንችል ያሳየና አዲስ ልምምድን ያመጣ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም