ኢትዮጵያ ለቀጣናው ልማትና ሰላም መረጋገጥ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለቀጣናው ልማትና ሰላም መረጋገጥ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው
ሮቤ ፤ የካቲት 28/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድን የሚያስተሳስሩ ግዙፍ የልማት ስራዎችን በማካሄድ ለቀጣናው ሰላም መረጋገጥ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር በሃሳብ ልዩነታችን ውስጥ የማንደራደርበት ቀይ መስመራችን ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅምን ያስከበረ ለአፍሪካ ቀንድ እና አጎራባች ሀገራት ትብብር፣ የጋራ ብልፅግና፣ ሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሰላምና የልማት አቅም በመሆን ረገድ ያለችበትን ሁኔታ በማስመልከት ኢዜአ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንን አነጋግሯል።
አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራንና ተመራማሪዎች እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ከማስከበር ባለፈ ለቀጣናው ብልፅግና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን አመልክተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የጂኦግራፊና አካባቢ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ፈዬ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ የሰላምና የልማት አቅም እየሆነች መምጣቷን ተናግረዋል።
በተለይ የአፍሪካ ቀንድ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ለንግድ እንቅስቃሴ ምቹ መሆኑን ተናግረዋል።
ቀጣናው ጥቂት የማይባሉ አካላት ፍላጎት ያለበት መሆኑንና ኢትዮጵያም ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያስጠብቅ መልኩ ከሀገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበር ቀጣናዊ ትስስርን የማጠናከር ጽኑ አቋሟን በተግባር እየገለጠች መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የስነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ክፍል መምህርና የቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ጉተማ አደም ናቸው።
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በማከናወን ከራሷ አልፎ ለአካባቢው አገራት የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት እየሰራች መሆኑን አመልክተዋል።
እንዲሁም ኢትዮጵያ ለህዝቧ ፍላጎትና ተጠቃሚነት ይበጃሉ ብላ የምትወስዳቸው የተለያዩ እርምጃዎች ከሷ አልፎ ለቀጣናው ልማትና ሰላም መረጋገጥ የሚጠቅሙ በመሆናቸው የመሪነት ሚናዋን እንድትወጣ እያስቻላት ስለመሆኑም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በብሪክስ ባለ ብዙ ወገን የትብብር መድረክ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ከራሷ አልፎ የአፍሪካን ድምጽ እያሰማች መሆኑን ያብራሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የማኔጅመንትና ኢኮኖሚክስ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ሁሳ አሎ ናቸው።
ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የልማት ጥረት በቀጣናውም ይሁን በአህጉሩ የስኬት መንገድ ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል።
እንዲሁም ኢትዮጵያ በተለይም በኃይል፣ በትራንስፖርት እና በሌሎች መሠረተ ልማቶች ለማስተሳሰርና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እያደረገች ያለው ጥረት በቀጣናው ያላትን የመሪነት ሚና ይበልጥ እንደሚያጠናክርም አክለዋል።