የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር በሃሳብ ልዩነታችን ውስጥ የማንደራደርበት ቀይ መስመራችን ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር በሃሳብ ልዩነታችን ውስጥ የማንደራደርበት ቀይ መስመራችን ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር በሀገራዊ የፖለቲካ የሃሳብ ልዩነታቸው ውስጥ ለድርድር የማይቀርብ ቀይ መስመር መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
ብሔራዊ ጥቅም የሀገርን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና የማኅበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚተለም የጋራ መሰረተ-ሕግና ታላቅ ሀገራዊ ግብ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በሚረዱ ፅንሰ ሀሳቦች ላይ ማተኮር ይጠበቅባቸዋል - ምሁራን
ለዚህም የአንድ ሀገር ዜጎች፣ መንግስትና የፖለቲካ አደረጃጀቶች በሃሳብ ልዩነት ውስጥ በዋና ዋና መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ የሚያችል የጋራ አቋም ሊይዙ ግድ ይላል።
ኢትዮጵያና ዜጎቿም በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና የቴክኖሎጂ መስኮች ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎቶችን የሚያስጠበቁ ሁለንተናዊ አቅም እየገነቡ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅትም በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል የባሕር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄና ሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ስኬታማነትም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር ጠንካራ ሀገረ መንግስት የሚያንጹ የጋራ አጀንዳዎችና መሰረቶች ናቸው።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደገለጹት፤ የሀገር ብሔራዊ ጥቅሞች በፖለቲካ እሳቤና የሃሳብ ልዩነቶች የማይገደቡ የሁሉም ዜጎች የማይታለፉ የጋራ አጀንዳዎች ናቸው ብለዋል።
የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነቢሃ መሐመድ፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ማስከበር በፖለቲካ የሃሳብ ልዩነት ውስጥ ለድርድር የማይቀርቡ ቀይ መስመሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ ሀገር የለንም ያሉት ኃላፊዋ፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጉዳይም ልዩነት ሊኖረን አይገባም ብለዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ማንኛውም የፖለቲካ አደረጃጀትና ዜጋ በአንድነት ሊቆሙለት የሚገባ የጋራ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።
የስምረት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የምክር ቤት አባልና የሚዲያና ኮምኑኬሽን ዘርፍ ምክትል ሰብሳቢ ጣዕመ አርዓዶም በበኩላቸው፤ ብሔራዊ ጥቅም ከማንኛውም የሃሳብ ልዩነቶች በላይ የጋራ አጀንዳ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር አጀንዳ በሃሳብ የበላይነት የተመሰረተ ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር ብሔራዊ ጥቅም ማስከበሪያ መሳሪያ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች በማንኛውም አይነት የፖለቲካና የሃሳብ ልዩነቶች ውስጥ ለድርድር ሊቀርቡ እንደማይገባ ተናግረዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ፓርቲያቸው የበኩሉን ገንቢ ሚና ለመወጣት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ሰለሞን ታፈሰም እንዲሁ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች በምንም አይነት መንገድ ለድርድር የማይቀርቡ የጋራ ጉዳዮቻችን ናቸው ብለዋል።
ለአብነትም የባሕር በር ባለቤትነት ማስከበርና ሀገራዊ ምክክር፣ ዘላቂ ልማትና ሰላም ግንባታ የኢትዮጵያ ለድርድር የማይቀርቡ የጋራ ብሔራዊ ጥቅሞች መሆናቸውን በመግለጽ።
በዚህም የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነትና ሀገራዊ ምክክር በስኬት በመቋጨት አስተማማኝ ዕድገትን የሚያስቀጥል ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡