ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በሚረዱ ፅንሰ ሀሳቦች ላይ ማተኮር  ይጠበቅባቸዋል - ምሁራን

ሆሳዕና ፤ የካቲት 28/2018 (ኢዜአ)፦ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በሚረዱ ፅንሰ ሀሳቦች ላይ ማተኮር  እንደሚጠበቅባቸው የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ገለፁ፡፡

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባን ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል

በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቅስቀሳ ጨምሮ የተለያዩ የቅድመ ምርጫ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ነው፡፡

ኢዜአ በፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ አካሄድ ዙሪያ ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ቆይታ አድርጓል።

ምሁራኑ በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሃገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በሚረዱ ጽንሰ ሃሳቦች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ አበራ ሄቢሶ እንዳሉት፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሀሳብን ይዘው በመቅረብ ሀገርን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጉዳዮችን ሊያነሱ ይገባል፡፡


 

የሀገረ መንግሥት ግንባታው የሚጠናከረው በሁሉም ኢትዮጵያውያን ይሁንታና ቅቡልነት በመሆኑ ገዥ ትርክትን በማስረጽ በጋራ ለመበልጸግ የሚደረገውን ጥረት ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከወገንተኝነት አስተሳሰብና ከፋፋይ ትርክት በመውጣት የህዝብ ፍላጎትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚረዱ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ላይ በማተኮር በህዝቡ ቅቡልነት ለማግኘት መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈጠረውን ምቹ ስነ-ምህዳር በመጠቀም ሃገራዊ ጥቅምን ያስቀደሙ ጽንሰ ሃሳቦች ላይ ማተኮር አለባቸው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሳምሶን ወልዴ ናቸው።፡


 

ለሀገርና ለህዝብ ጠቃሚ የሆኑ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለህዝቡ በማቅረብ  በውድድሩ ተቀባይነትን ለማግኘትና ለጋራ ተጠቃሚነት መረጋገጥ መስራት ከተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ይጠበቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ወር  የሚቆይ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም