በዞኑ በፍራፍሬ ልማት የተገኘውን ውጤት የበለጠ ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በፍራፍሬ ልማት የተገኘውን ውጤት የበለጠ ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ነቀምት ፤ የካቲት 28/2018 (ኢዜአ)፦በምስራቅ ወለጋ ዞን በፍራፍሬ ልማት የተገኘውን ውጤት የበለጠ ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦትን በውስጥ አቅም ለመሸፈን በመቻሉ ለበልግ እርሻ ምቹ ሁኔታን ተፈጥሯል
በጽሕፈት ቤቱ የቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ ቡድን መሪ አቶ አሰፋ መኮንን ፤ በዞኑ ለፍራፍሬ ልማት የሚመች የግብርና መሬት እንዳለ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለልማቱ በተሰጠው ትኩረት የፍራፍሬ ልማት ሥራ በስፋት እየተተገበረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ለዚህም የዞኑ አርሶ አደሮች ከመደበኛ የሰብል ልማት በተጓዳኝ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ እና ሌሎችንም የተመረጡ የፍራፍሬ ዓይነቶች እንዲያለሙ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ያለውን ምቹ ሥነ-ምህዳር፣ የአየር ንብረት እና በቂ የውኃ ሀብት በመጠቀም እስካሁን 15 ሺህ 371 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ማልማት መቻሉን አስታውቀዋል።
የፍራፍሬ ምርት እየለማበት ከሚገኘው ሄክታር መሬት ውስጥ ከፊሉ ምርት መስጠት መጀመሩን ጠቅሰው፤ በ2017/2018 ምርት ዘመን ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ የፍራፍሬ ምርት ተሰብስቦ ለገበያ መቅረቡን አብራርተዋል።
የፍራፍሬ ምርቱ በአመዛኙ በጉደያ ቢላ፣ ጎቡ ሰዮ፣ ሲቡ ስሬ እና ጉቶ ጊዳ ወረዳዎች የተመረተ ሲሆን፤ የልማቱ ተሳታፊ አርሶ አደሮች የፍራፍሬ ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ገልጸዋል።
የፍራፍሬ ልማቱን ለማስፋፋት የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ ተግባራዊ መደረጉን አንስተው፤ በየደረጃው በሚገኙ ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎችም የፍራፍሬ ችግኞች በተደራጀ መልኩ በጥራትና በብዛት እየተዘጋጁ ለልማቱ ተሳታፊዎች ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን አውስተዋል።
በምስራቅ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዮ ወረዳ ከልማቱ ተሳታፊዎች መካከል አርሶ አደር ስዒድ ጂላሉ በሰጡት አስተያየት፤ ባላቸው አንድ ሄክታር ይዞታ ላይ አቮካዶና ሙዝ በማልማት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የፍራፍሬ ምርታቸውን ከሀገር ውስጥ ገበያ ባለፈ መንግሥት ባመቻቸላቸው የገበያ ትስስር በመጠቀም ካለፈው ዓመት ወዲህ 33 ኩንታል አቮካዶ ወደ ውጭ ሀገር በመላክ 150 ሺህ ብር ትርፍ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ከሙዝ ልማት ጋር በተያያዘም በስፋት ሥራ ውስጥ መግባታቸውን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ የደረሰ ሙዝ በመሰብሰብ ለገበያ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ሌላኛው በዞኑ ጉቶ ጊዳ ወረዳ አርሶ አደር ሀብታሙ ደጀኔ በበኩላቸው፤ በየዓመቱ ከሚያመርቱት አቮካዶ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት በሰብል ምርት ላይ ብቻ በመሰማራት የሚያገኙት ገቢ ውስን እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን ባገኙት ምርጥ ዘር እና ድጋፍ በመጠቀም ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ 20 ኩንታል አቮካዶ ምርት በመሰብሰብ ለገበያ ማቅረባቸውን አውስተዋል።
እንደ አርሶ አደሮቹ ገለጻ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት የተሻለ ገቢ ከማስገኘት ባለፈ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሥርዓተ ምግብ ለማሻሻል አስችሏቸዋል።