ቀጥታ፡

በክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦትን በውስጥ አቅም ለመሸፈን በመቻሉ ለበልግ እርሻ ምቹ ሁኔታን ተፈጥሯል

ዲላ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምርጥ ዘር አቅርቦትን በውስጥ አቅም ለመሸፈን በመቻሉ በበልግ እርሻ የግብዓት ስርጭትን ውጤታማ ማድረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ የብድር አቅርቦትን ጨምሮ ትራክተርና ሌሎች የግብርና ግብዓቶችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የሚታረስ መሬትን ለማስፋትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።

የቢሮው ምክትልና የግብርና ግብዓት ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዘርፍ ኃላፊ ግዳልቅ አልቅሚ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ የበልግ ዝናብ ፈጥኖ መጀመሩን ተከትሎ የግብዓትና ቴክኖሎጂ ስርጭት ስራ ተጀምሯል።

በዚሁ ወቅት ከ287 ሺህ ኩንታል በላይ ዳፕና ዩሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንና ከዚህ ውስጥ 160 ሺህ 64 ኩንታል ማዳበሪያ ስርጭት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ለበልግ እርሻ ከሚያስፈልገው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 56 በመቶውን የሚሸፍን ሲሆን ቀሪ ስርጭትም በቀጣይ ሳምንት እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በተለይ ለበቆሎ፣ ለማሽላ፣ ለማሾ፣ ለቦሎቄ፣ ጤፍን ጨምሮ ለዋና ዋና ሰብሎች ከሚያስፈልገው 65 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ውስጥ 63 ሺህ 560 ኩንታል ምርት በማምረት በየማዕከላቱ ቀድሞ ማከማቸት መቻሉን አስረድተዋል።

በዘንድሮው ዓመትም የ37 ትራክተሮች ግዢ መፈፀሙን የተናገሩት ኃላፊው በአጠቃላይ ለበልግ እርሻ 415 ትራክተሮች  ወደ  ስራ መሰማራታቸውን አስረድተዋል።

በበልግ እርሻ በአዝርዕት፣ በአትክልትና ስራስር ሰብሎች ከሚለማው 987 ሺህ 314 ሄክታር መሬት ውስጥ 209 ሺህ 366 ሄክታሩ በትራክተር እየታረሰ መሆኑንም ነው ያነሱት።

ይህም በክልሉ ሜካናይዘሽንን በማስፋት የአርሶ አደሩን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

የበልግ ወቅት የክልሉ ዋና የእርሻ ጊዜ በመሆኑ አርሶ አደሩ ያገኘውን ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በአግባቡ ስራ ላይ በማዋል ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ መስራት አንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም