ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ለሀገራዊ ደህንነትና ለቀጣናዊ ሰላም መከበር ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ሀገራዊ ደህንነትን ለማረጋገጥና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ወሳኝ መሆኑን የቀድሞ የባህር ኃይል አባልና የታሪክ ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተገቢና ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያለው ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ ጥረት እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያና ቀይ ባህር ለዘለዓለም ተነጣጥለው እንደማይኖሩ በማንሳት፥ ፍትሐዊ ጥያቄያችን በሰላማዊ፣ በሰጥቶ መቀበልና በድርድር መርህ ምላሽ እንዲያገኝ ጥረታችን ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ ፍትሐዊ ካልሆነ በዓለም ላይ ፍትሕ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጊዜ ጉዳይ እንጂ መልስ ማግኘቱ አይቀሬ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቀድሞ የባህር ኃይል አባል ጁኒየር ሌተናንት ሀለፎም መሰለ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በሴራ የባህር በር አልባ እንድትሆን ከመደረጓ በፊት በአካባቢው ላይ ጠንካራና ተፅዕኖ ፈጣሪ የባህር ኃይል ነበራት።


 

በዚህም በቀይ ባህር ቀጣና የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሌሎች ሀገራት የንግድ መርከቦች ጭምር ደህንነታቸው ተጠብቆ ሰላማዊ ጉዞ እንዲያደርጉ ሀገሪቱ ወሳኝ ሚና ስትጫወት መቆየቷን አስታውሰዋል።

የባህር ኃይሉ በተለይም ሕገ-ወጥ ንግድ፣ ኮንትሮባንድን፣ የባህር ላይ ሽፍቶችን እንቅስቃሴዎች በመግታት ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ዋስትና ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።

በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የህልውና ጉዳይ ለሆነው የባህር በር ጥያቄ ዘላቂ ምላሽ ለማግኘት ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር በማጣቷ ምክንያት ከፍተኛ ዋጋ የከፈለች መሆኑን ጠቅሰው፤ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቀደም ብሎ ሊነሳ የሚገባው እንደነበር አንስተዋል።


 

የታሪክ ምሁርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ በበኩላቸው፤ የጥንቶቹ የዳማትና የአክሱም ሥልጣኔዎች ከባህር በር ጋር በነበራቸው ቁርኝት የገነኑ እንደነበሩ በታሪካዊ ማስረጃነት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ባህር በር መመለሷ ሀገራዊ ተጽዕኖዋን ከመጨመሩ በላይ ብሔራዊ ጥቅሟን በዓለም አቀፍ መድረክ ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ጉልህ አሻራ እንደሚያሳርፍ አክለዋል።


 

የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ድልና በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያሳዩትን ጽኑ አንድነት የባህር በር ጥያቄው ግቡን እንዲመታና ብሔራዊ ጥቅሟ እንዲከበር በአንድነት በመቆም ሊደግሙት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም