ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተገቢና ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተገቢና ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን በኢትዮጵያ የኖርዌይ እና የባንግላዲሽ አምባሳደሮች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ኢትዮጵያና ቀይ ባሕር በሕግ፣ በመልክዓምድር፣ በታሪክና ሌሎች መለኪያዎች ሊነጣጠሉ እንደማይችሉ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ስቲያን ክሪስቴንሰን እና በኢትዮጵያ የባንግላዲሽ አምባሳደር ኤር ቫይስ ማርሻል ሲትዋት ናይም ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የጋራ ዕድገትን ለማረጋገጥ አስተማማኝ የባሕር በር ወሳኝ ነው።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋን ምላሽ ለማስገኘት የምትከተለው ሕጋዊ፣ ሰላማዊና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ሀገሮቻቸው እንደሚገነዘቡም አምባሳደሮቹ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄና የባሕር በርና የአማራጭ ወደብ አገልግሎት ለጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ስቲያን ክሪስቴንሰን፤ ኢትዮጵያ በአስደናቂ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የምትገኝ ከፍተኛ የመልማት አቅም ያላት ሰፊ ሀገር ናት ብለዋል።

ይህንን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚመጥን አስተማማኝ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ጉልህ ፋይዳ ያለው ሀገራዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን አስተማማኝ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ አስፈላጊነት በቅጡ እንረዳለን ያሉት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያም በቀጣናው ሀገራት የባሕር በር ማግኘት የምትችልበት ሰፊ ዕድል መኖሩን ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ የባንግላዲሽ አምባሳደር ኤር ቫይስ ማርሻል ሲትዋት ናይም፤ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የንግድና ኢንቨስትመንት፣ ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ የባሕር በር አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም እያደገ ከሚገኘው የንግድና ኢንቨስትመንት የኢኮኖሚ ዕድገቷ አንጻር ሕጋዊነቱን እንደሚያጎላው አንስተዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ምላሽ ለማስገኘት ከቀጣናው ሀገራት ጋር በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም