ቀጥታ፡

በክልሉ የግብርና ልማት ስራዎችና የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ተመራጭ የሥራ እድል መፍጠሪያ ሆነዋል

ዲላ ፤ የካቲት 28/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ልማት ስራዎችና የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ተመራጭ የሥራ እድል መፍጠሪያ እየሆኑ መምጣታቸውን የክልሉ የሥራና ክህሎት ቢሮ ገለጸ።

አካባቢያዊ አቅምን በአግባቡ መጠቀም ለዘላቂ መፍትሔ ትልቅ መሰረት ነው

በጌዲኦ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በሌማት ትሩፋት፣ በማኑፋክቸሪንግና ተኪ ምርቶች የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች የስራ እንቅስቃሴ ምልከታ ተካሄዷል፡፡


 

በወቅቱም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በክልሉ የግብርና ልማት ስራዎችና የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ተመራጭ የሥራ እድል መፍጠሪያ እየሆኑ ነው፡፡

በተለይ ለክህሎት መር የሥራ እድል ፈጠራ በተሰጠው ልዩ ትኩረት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት አዋጭ በሆኑ ዘርፎች ወጣቶችን በማሰልጠን ወደ ሥራ እንዲገቡ በተደረገ ጥረት ውጤት መገኘቱን አንስተዋል።

በክልሉ በገጠር ወረዳዎች ስድስት ሄክታር እንዲሁም በከተማ አንድ ሄክታር መሬት ለሥራ ፈላጊ ወጣቶች በማቅረብ መሰረታዊ የሥራ እድል ፈጠራ ግቦች መሳካታቸውንም ገልጸዋል።


 

በክልሉ የግብርናና የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ አዋጭና ተመራጭ የሥራ እድል ፈጠራ ዘርፍ መሆኑን አንስተው  በግማሽ ዓመቱ ብቻ በተለያዩ ዘርፎች ከ163 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩንም ተናግረዋል።

በቀጣይም የአካባቢውን ጸጋ መሰረት ያደረገ የስራ እድል በመፍጠር የኢንተርፕራይዞችን ልማት ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ እና የመስክ ምልከታውም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።

በዞኑ ባለፉት 6 ወራት ወደ 11 ሺህ ለሚጠጉ ወጣቶች ቋሚ የስራ እድል መፈጠሩን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ  ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ናቸው።


 

በተለይ የአካባቢውን ጸጋ መሰረት በማድረግ ሰፊ መሬት በማይጠይቁ የሌማት ትሩፋት ዘርፎች ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት መቻሉን ጠቅሰው በዚህም ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

ኢቶስ የወተት ላሞች እርባታና የመኖ ግብርና ኢንተርፕራይዝ ስራ አስኪያጅ አቶ ተካልኝ ዓለማየሁ በበኩላቸው፤ ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት በዲላ ከተማ በሁለት የወተት ላሞች የጀመሩት እርባታ ዛሬ ላይ ከ12 በላይ መድረሱን ተናግረዋል።


 

ከአንዲት ላም በአማካይ ከ18 ሊትር በላይ ወተት እንደሚያገኙ አንስተው ይህንንም ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከወተት አቅርቦት ባለፈ በሶስት ሄክታር መሬት ላይ መኖን በዘመናዊ መንገድ በማልማት ለወተት ላሞቹ ከመመገብ አልፈው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በወተት ላም፣ በዶሮ እርባታና በማር ልማት በተቀናጀ ግብርና ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸውን ያሱት ደግሞ በወናጎ ወረዳ መኮኒሳ ቀበሌ የበጸሎት የተቀናጀ ግብርና ኢንተርፕራይዝ ስራ አስኪያጅ ሀገረ ሰላም በርሱ ናቸው።

የእንስሳት ተዋጽኦዎችን በተለይ ወተትና እንቁላል እንዲሁም ዶሮ ለአርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም