ቀጥታ፡

አካባቢያዊ አቅምን በአግባቡ መጠቀም ለዘላቂ መፍትሔ ትልቅ መሰረት ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27 /2018(ኢዜአ)፦ የአካባቢያዊ አቅሞችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እና ራስን ለመቻል ወሳኝ መሆኑን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ገለጹ።

5ኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት "ራስን መቻል ለዘላቂ ሰላምና አካታች ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬሽን ሴንተር ትናንት መከፈቱ ይታወቃል።

የዚሁ መርሃ ግብር አካል የሆነ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።


 

አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የአካባቢያዊ አቅምን ለሰብዓዊ ድጋፍ ማሳደግ የዚህ ዓመት ብቻ ሳይሆን የቀጣይ ዓመታት ቀዳሚ አጀንዳ ነው፡፡

እውነተኛ ለውጥ የሚመጣው ሀብትን ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወደ አገር በቀል ድርጅቶች በማዛወር ብቻ ሳይሆን አባወራዎችንና ማህበረሰቡን የሂደቱ ባለቤት በማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

ማንኛውም አደጋ ሲከሰት የመጀመሪያው ምላሽ ሰጪ ራሱ ማህበረሰቡ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ አዲሱ ስትራቴጂ ትኩረቱን ከታች ወደ ላይ በሚመጣ ንቅናቄ ላይ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ የምግብ እህል ክምችት እና ጠንካራ የሎጂስቲክስ ስርዓት ለመገንባት በከፍተኛ ሁኔታ ኢንቨስት እያደረገች መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ዓለም አቀፍ አጋሮችም በማህበረሰብ አቅም ግንባታ እና በልማት ስራዎች ላይ በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው፤ የሀገር ራስን የመቻል ጉዞ እውን ለማድረግ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚሰሯቸው ስራዎች ከሀገሪቱ የፖሊሲ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር መጣጣም ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ራስን መቻል ሲታሰብ አካባቢያዊነት ማዕከላዊ ነጥብ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ከልማት ዕቅዶች ጋር በተጣጣመ መልኩ ተግባራዊ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።


 

ከተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ፅዮን አለምሰገድ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ አካባቢያዊ አቅምን በአግባቡ ለመጠቀም የመንግሥት ተቋማት ሚና ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ጠቅሰዋል።

ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆንም የተለያዩ ተቋማት የተቀናጀ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም