በዞኑ የሌማት ትሩፋት ተሳታፊዎች ምርታቸውን ከፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የሌማት ትሩፋት ተሳታፊዎች ምርታቸውን ከፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል
ጊምቢ ፤ የካቲት 28/2018 (ኢዜአ)፦በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በመሳተፍ ምርታቸውን ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን እያሳደጉ መሆኑን በምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ የሚገኙ ወጣቶችና ሴቶች ገለጹ።
በዞኑ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማሳደግ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት በበኩሉ በበጀት ዓመቱ መርሃ ግብሩን ለማስፋፋትና ለማጠናከር ከ3 ሚሊዮን በላይ የአንድ ቀን ጫጩቶችና ቄብ ዶሮዎች፣ 100 ሺህ የሚጠጋ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ማሰራጨቱን አስታውቋል።
በቤጊ ወረዳ የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል እስራኤል ብሩሴና ዮሐንስ ዘሪሁን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በማህበር ተደራጅተው በሌማት ትሩፋት የተሻሻሉ የወተት ላም ዝርያ በማርባት ተጠቃሚ ሆነዋል።
እንደ ወጣቶቹ አስተያየት እያረቧቸው ካሉት የተሻሻሉ አምስት የወተት ላሞች በቀን ከ50 ሊትር በላይ ወተት ያመርታሉ።
ምርቱንም ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
በተለይ የወተት ምርቱን በወረዳው ለሚገኙ ሆቴሎች፣ ካፌዎችና ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ስለሚያቀርቡ የገበያ ችግር እንዳላጋጠማቸው ገልጸው ከሽያጩም በወር በአማካኝ ከ25 ሺህ እስከ 30 ሺህ ብር የተጣራ ትርፍ እንደሚያገኙ አስረድተዋል።
ገቢያቸውን በመቆጠብና ሥራቸውን በማስፋፋት ለሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ እንዳላቸውም አስታውቀዋል።
በቤጊ ወረዳ የኮቦር ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዘነበች ዲቢሳ በኩላቸው፤ በሌማት ትሩፋት የዶሮ ጫጩት ማሳደግ እና ማከፋፈል ሥራ ላይ በማህበር ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ይናገራሉ።
በከተማ አስተዳደሩ በተደረገላቸው የሼዶች ድጋፍ አሁን ላይ አንድ ሺህ የአንድ ቀን ጫጩቶችን ተረክበው በማሳደግ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው በቀጣይ እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማርባት ተጠቃሚነታቸውን ለማስፋት እየሠሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የምዕራብ ወለጋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈይሳ ሀምቢሳ፤ በዞኑ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተግባራዊ በመሆኑ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አስተዋፅኦ ከማበርከቱ ባለፈ ለብዙዎች የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን በተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን አውስተዋል።
ጽሕፈት ቤቱ ልማቱን ለማጠናከርና ለማስፋፋት የዶሮ ጫጩቶች፣ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የወተት ላሞችና የንብ ቀፎ ለመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች ማቅረቡን አመልክተዋል፡፡
በዚህ ረገድ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ በዶሮ እርባታ ለተሰማሩ ነዋሪዎች 3 ሚሊዮን 250 ሺህ በላይ የአንድ ቀን ጫጩቶችና ቄብ ዶሮዎች፣ 100 ሺህ የሚጠጋ ዘመናዊ የንብ ቀፎ መሰራጨቱን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት የተሰራጩ የተሻሻሉ ጊደሮችን በሰው ሠራሽ ዘዴ በማዳቀልም 24 ሺህ ጥጆች ተወልደው እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አብራርተዋል።