በዞኑ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማሳደግ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማሳደግ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
ደብረ ማርቆስ ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦በምስራቅ ጎጃም ዞን የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማሳደግ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የዞኑ እንስሳትና ዓሳ ሃብት መምሪያ አስታወቀ።
በዞኑ በበጀት ዓመቱ ከእጣንና ሙጫ ምርት ሽያጭ ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ትኩረት ተደርጓል
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ዳኘ ዋሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተግባራዊ መደረጉ የእንስሳት ልማቱን በግብዓትና በአዳዲስ አሰራር ለማገዝ አስችሏል።
በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራትም ከ33 ሺህ በላይ በሚሆኑ ላሞች ላይ የዝርያ ማሻሻል ተግባር መከናወን መቻሉን ጠቁመው በዚህም አርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ዝርያ የማሻሻል ስራው በኮርማ፣ በተፈጥሮ ድሪና በሆርሞን መሆኑን ጠቁመው በማዳቀል ስራው ከ17 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
ዝርያ የማሻሻል ስራ መከናወኑ ከነባር ላም በቀን ይገኝ የነበረውን አንድ ነጥብ ስምንት ሊትር ወተት ከ10 ሊትር በላይ ለማሳደግ ማስቻሉን ጠቁመዋል።
የስጋ ምርታማነትን ከማሳደግ አንፃርም በተከናወኑት ተግባራት እስከ 30 ኪሎ ግራም ጭማሪ ምርት ማግኘት እንደተቻለም አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ የተከናወነው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ስራ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ40 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለውም ተገልጿል።
አፈጻጸሙ ባለሙያዎች ቀበሌ ድረስ ወርደው በመስራታቸው የመጣ ውጤት ነው ብለዋል።
ከተጠቃሚዎች መካከል የማቻከል ወረዳ የውላ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገነቱ ገላጋይ እንዳሉት ፤በሁለት ላሞቻቸው ላይ በተካሔደው ዝርያ የማሻሻል ስራ በቀን ከ20 ሊትር በላይ ወተት እያገኙ ነው።
ያገኙትን ጥቅም ይበልጥ ለማሳደግም በዚህ ዓመት ሁለት ላሞችን በኮርማ ማዳቀላቸውን ተናግረዋል።
በዚሁ ወረዳ የአማሪ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ዘላለም ሲሳይ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል ዝርያዋን ካሻሻሏት አንዲት ላም እስከ 12 ሊትር ወተት በቀን በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል።
በዘንድሮ ዓመትም በሶስት ጊደሮች ላይ የዝርሻ ማሻሻል ስራ መስራታቸውን ነው የገለጹት።
የወተት ምርት ለማህበራት በማስረከብ የምግብ ፍጆታቸውን ከመሸፈን አልፎ ተቀማጭ ገንዘብ እንዲኖራቸው ማድረጉን ተናግረዋል።
በዞኑ እስከ 200 ሺህ የሚደርሱ ዝርያቸው የተሻሻሉ እንስሳት እንደሚገኙ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።