አርሶ አደሩ በበልግ ወቅት የሚጠበቀውን የዝናብ ስርጭት ተጠቅሞ የሰብል ምርታማነቱን ማሳደግ አለበት - ኢዜአ አማርኛ
አርሶ አደሩ በበልግ ወቅት የሚጠበቀውን የዝናብ ስርጭት ተጠቅሞ የሰብል ምርታማነቱን ማሳደግ አለበት
ደሴ ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦አርሶ አደሩ በበልግ ወቅት የሚጠበቀውን መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ተጠቅሞ የሰብል ምርታማነቱን ማሳደግ እንዳለበት በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የምስራቅ አማራ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል አስታወቀ።
በጋምቤላ ክልል ወይና ደጋማ አካባቢዎች የሚኖረው የዝናብ ስርጭት ለበልግ እርሻ አመቺ ነው
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ በበኩሉ ከ104 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበልግ ዝናብ ለማልማት መታቀዱን አስታወቋል።
በማዕከሉ የትንበያና ቅደመ ማስጠንቀቂያ ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ ሉባባ መሀመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በልግ ለምስራቅ አማራ ቀጠና ከመኸር ቀጥሎ 2ኛው የምርት ወቅት ነው።
ከተያዘው ወር መጨረሻ ጀምሮ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖችን ጨምሮ ምስራቅ አማራ ቀጠና መደበኛና ከመደበኛ በላይ የበልግ ዝናብ ይጠበቃል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም በደቡብ ወሎ እና በሰሜን ወሎ ዞን ዝናብ መጣል መጀመሩን ጠቁመው፣ አርሶ አደሩ በበልግ የሚጥለውን ዝናብ በመጠቀም የዘር ሥራውን አጠናከሮ ማስቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
ለዚህም የበልግ ዝናብን በማሳው ዳርና ውስጥ ላይ በማቆር በደረቅ ወቅት ለመጠቀም የሚያስችል ዝግጅት እንዲያደርግም መክረዋል።
እንደሃላፊዋ ገለጻ ፤የበልግ ዝናብ ለሰብል ልማት፣ የአፈር እርጥበትን ለማሻሻል፣ ለእንስሳት ግጦሽ፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።
ቅጽበታዊ ጎርፍ፣ የሰብል በሽታና ተባይ ተከስቶ ጉዳት እንዳይደርስ አርሶ አደሩ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም አሳሰበዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ በበኩላቸው፤በዞኑ በበልግ ወቅት ከ104 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል እንደሚለማ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የበልግ ዝናብ በአካባቢው መዝነብ መጀመሩን ገልጸው፣ አርሶ አደሩም የዘር ሥራውን አጠናክሮ በማስቀጠል ምርታማነቱን እንዲያሳድግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በበልግ እርሻ ምርታማነትን ለማሳደግም ለአርሶ አደሩ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና ሌሎች ግብአቶችን የማቅረብ ሥራ መሰራቱን አመልክተዋል፡፡
በበልግ ልማት እየተሳተፉ ካሉ የደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ኢብራሂም በሽር፤ አንድ ሄክታር ማሳቸውን በበልግ ለማልማት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በእስካሁኑ የልማት ሥራም ለበልግ ያዘጋጁትን የተፈጥሮ ማዳበሪያ አለስልሰው ባዘጋጁት ማሳ መበተናቸውን ገልጸው፣ በመንግስት ሰው ሰራሽ ማዳበሪያም እንደቀረበላቸው ተናግረዋል።
በዚሁ ዞን የለጋምቦ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ይማም አሊ በበኩላቸው፤ አንድ ሄክታር ተኩል ማሳቸው ላይ በበልግ ስንዴ፣ ገብስና ምስር ለማልማት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።