በጋምቤላ ክልል ወይና ደጋማ አካባቢዎች የሚኖረው የዝናብ ስርጭት ለበልግ እርሻ አመቺ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ወይና ደጋማ አካባቢዎች የሚኖረው የዝናብ ስርጭት ለበልግ እርሻ አመቺ ነው
ጋምቤላ ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ወይና ደጋማ አካባቢዎች በቀጣዮቹ ሶስት ወራት የሚኖረው የዝናብ ስርጭት ለበልግ እርሻ አመቺ መሆኑን በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የጋምቤላ ክልል ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል አስታወቀ።
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ ሀገራት ለዓለም አቀፍ ቃል ኪዳኖች ተፈፃሚነት በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል
በኢንስቲትዩቱ የጋምቤላ ክልል የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋሁን ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ወይና ደጋማ አካባቢ በቀጣይ ወራት የሚኖረው የበልግ ዝናብ ለእርሻ ስራ ተስማሚ ነው።
በክልሉ ወይና ደጋማ የአየር ፀባይ ያለው የማጃንግ ዞን በቀጣዩቹ ሶስት ወራት የሚኖረው የዝናብ ስርጭት ለእርሻ ስራና ለእንስሳት ግጦሽ አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር የአየር ትንበያ መረጃ ያመለክታል ብለዋል።
በተለይም በዞኑ ቀድመው ለሚዘሩ የሰብል ዓይነቶችና ለመኸር እርሻ ስራ ዝግጅት በቂ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር መተንበዩን አመላክተዋል ።
በሌላ በኩል ደግሞ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች ጠንከር ያለ የሙቀት መጠን እንደሚኖር የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ገልጸዋል።
በመሆኑም የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር የውሃ መጠን መቀነስ ሊኖር ስለሚችል ህብረተሰቡ ውሃን በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት ምክር ሃሳብ ሰጥተዋል።
እንዲሁም ከሙቀቱ መጨመር ጋር ተያይዞ በሰዎች ላይ የቆዳ ሽፍታ ሊከሰት ስለሚችል ማህበረሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።