በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጁ ነን - የኢሉአባቦር ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጁ ነን - የኢሉአባቦር ዞን ነዋሪዎች
መቱ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦ ዘንድሮ በሚካሄደው በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት መሳተፍ የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን በኦሮሚያ ክልል የኢሉአባቦር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።
ካርድ ወስደን በመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለመጠቀም ተዘጋጅተናል -የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓም የሚካሔደው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የተለያዩ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ እየሰራ ይገኛል።
ከዝግጅቶቹ መካከል ከነገ የካቲት 28/2018 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሔደው የመራጮች ምዝገባ ተጠቃሽ ነው።
ቦርዱ በአጠቃላይ ከሚኖሩት የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በ17ሺህ ያህሉ የዲጂታል የመራጮች ምዝገባን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
በኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቦር ዞን የሁሩሙ ወረዳ ነዋሪዋ ህዝባለም ደገፉ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ መብቴን ለመጠቀም የመራጭነት ካርድ ለመውሰድ እየተጠባበኩ ነው ብለዋል።
የመቱ ወረዳ ነዋሪዋ ዝማርጉ ጀማል እና ናሐዊ ደፋር በበኩላቸው፤ በመራጭነት ተመዝግበው መብታቸውን ለመጠቀም እንዲችሉ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ምርጫ ለሀገረ መግሥት ግንባታ ወሳኝ ምእራፍ በመሆኑ የዜግነት ግዴታዬን በኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነኝ የሚለው ደግሞ የመቱ ከተማ ነዋሪው ወጣት በፈቃዱ እንዳለ ነው።
ወጣት ፌዴሳ ታረቀኝ እና ግርማ ፍሪሳ በበኩላቸው፤ ጠቅላላ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንደ ወጣት የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
በሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ ሴቶችና ወጣቶች የሚኖራቸው ሚና የላቀ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን በመገንዘብ የምርጫ ካርድ በመውሰድ የሚወክለንን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
በተለይም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ዘርፎች ዘላቂ ተጠቃሚነታችን የሚያረጋግጥልን ፓርቲ ወደ ስልጣን ለማምጣት የመራጮች ምዝገባ እስኪጀመር እየጠበቅን ነው ብለዋል።