ካርድ ወስደን በመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለመጠቀም ተዘጋጅተናል -የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ካርድ ወስደን በመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለመጠቀም ተዘጋጅተናል -የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች
ሚዛን አማን፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦ ለምርጫው ካርድ በመውሰድ ይበጀናል የሚሉትን የመምረጥ ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ከነገ ጀምሮ ይካሄዳል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሻለ ሀሳብ ያለው ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - ነዋሪዎች
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች፤ ለምርጫው ካርድ በመውሰድ ይበጀናል የሚሉትን አካል የመምረጥ ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ይረፉ መሸሻ ፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም የሚሰራ ፓርቲን ለመምረጥ ከወዲሁ ዝግጅት እያደረግን ነው ብለዋል።
በምርጫው በመሳተፍ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ እንደሚወስዱም ገልጸዋል፡፡
ወይዘሮ ሶስና ሀብተማርያም የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው፤ በምርጫ መሳተፍ ሕገ መንግስቱ የሰጠን ዲሞክራሲያዊ መብት መሆኑን በመረዳት እየተዘጋጀን ነው ብለዋል።
የሚወክለኝን ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሐ ግብር መሠረት ተመዝግቤ ካርድ ለመውሰድ ተዘጋጅቻለሁ ነው ያሉት።
የሀገረ መንግሥት ግንባታን የማጠናከር አንዱ አካል የሆነው የምርጫ ሥርዓት ላይ መሳተፍ ከአንድ ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ያለው ደግሞ ወጣት መልካሙ አሰፋ ነው።
ከሕዝብ ጋር ሆኖ የተሻለች ኢትዮጵያን ይፈጥራል የሚለውን ፓርቲ ለመምረጥ በሀሳብ ላይ የተመሠረተ ዝግጅት ማድረጉን ተናግሯል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ አለማየሁ ሻርንስ ምርጫ ዜጎች የሀገራቸው የነገ ዕጣ ፈንታ ላይ የሚወስኑበት ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት የሚመሠረተው በምርጫና ምርጫ ብቻ በመሆኑ ለአካባቢ ልማትና ዕድገት የተሻለ አማራጭ ይዞ የሚመጣን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
ኢዜአ ተዘዋውሮ እንደተመለከተው ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሚዛን ተፈሪ ምርጫ ክልል በተለያዩ ቀጠናዎች የምርጫ ጣቢያ የማደራጀት ሥራ ተከናውኗል።